የውስጥና የውጭ ጠላቶች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ለመናድና የአገሪቱን ህዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍ እያደረጉ ያለው ጥረት እንደማይሳካ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አስገነዘበ፡፡
በነገው እለት የሚከበረው 42ኛው ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስገነዘበው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድና የህዳሴ ጉዞውን ለማደናቀፍ ያላሳለሰ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ሊሳካላቸው አልቻለም ለወደፊቱም አይችልም ብሏል።
ዕለቱ የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት በጋራ በመሆን የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት ዳግም ቃል የሚገቡበት በዓል እንደሚሆን መግለጫው ጠቁሟል።
ካለፉት ዓመታት የህዳሴ ጉዞ ልምድና ትምህርት በመውሰድ "አሁንም ድርጅቱን በጥልቀት በማደስ ለተልዕኮው ብቁ እናደርገዋለን" በሚል መሪ ሐሳብ በዓሉ እንደሚከበርም መግለጫው ገልጿል።
ህወሓት 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከቀደሙት በዓላት የሚለየው ድርጅቱ የ15 ዓመታት የህዳሴ ጉዞውን በጥልቀት በገመገመበት ማግስት መከበሩ እንደሆነም ተጠቁሟል።
መግለጫው አያይዞም ህወሓት በሰፊ ህዝባዊ መሰረት የጸና በሳይንሳዊ መርህና ተግባር የበለጸገ እና ፖለቲካዊ ብቃቱን ያስመሰከረ መሪ ድርጅት መሆኑን ጠቁሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችን በብቃት በመሻገር አንጸባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ የመጣ ድርጅት መሆኑን አስገንዝቧል ፡፡
አሁንም በሀገሪቱ እየተፈጠረ ካለው ሀብትና ዕድገት አንጻር በርካታ ተግዳሮቶችም አብረው መምጣታቸውን ገልጾ ህወሓት ፈተናዎች ሲያጋጥሙት በጥልቀት በመታደስ የመፍታት ልምዱን ተጠቅሞ ከህዝቡ ጋር እንደሚፈታው አስገንዝቧል ።
የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን የአገሪቱን ህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ ህወሓት ትግሉን በጽናት እንደሚቀጥል መግለጫው አስታውቋል፡፡
በገጠር ግብርና መር የሆነው የሃገሪቱ ፖሊሲ የክልሉ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከማድረግ ባለፈ ጥሪት እንዲቋጥሩ እያስቻለ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው አንስቷል ።
በከተሞችም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ሀብት ማፍራት መጀመራቸው የጠቀሰው መግለጫው፤ ከተሞች የኢንቨስትመንት ምንጭ እና ለኢንዱስትሪ መደላድል መሆን መጀመራቸውን አስረድቷል ።
በድህነት የዓለም ተምሳሌት ተደርጋ ትታይ የነበረችው አገራችን አሁን ፈጣን ፣ ፍትሃዊ ልማትና ሰፊ መሰረት ያለው ዲሞክራሲ ለመገንባት ርብርብ ላይ መሆኗን ነው ያመለከተው ህወሓት በመግለጫው፡፡