ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ( ህወሃት) የተመሠረተበትና ትጥል ትግል የጀመረበት 42ኛው የህወሃት ምስረታ በዓል በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በስዊዘርላንድ ሎዛን ከተማ በድምቀት ተከበረ ።
በምስረታ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ከተማ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ካሳዬ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የዘንድሮ የህወሃት የምስረታ በዓል የሚከበረው የፌደራሉ ሥርዓትና ልማታዊ መሥመር የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለአገሪቱ አንድነትና ቀጣይ ልማት ወሳኝ መሆኑ ጎልቶ በወጣበት ወቅት ሆነን ነው ብለዋል ።
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ በክብርና በጽናት ያለፉት ሰማዕታት አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት በመራራ ትግል በመገርሰሳቸው ምክንያት ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትን በማረጋገጥ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ።
በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙትን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የትምክህት፣ የጠባብነት አመለካከት አደጋዎችን ለመከላከል በመላ አገሪቱ እየተካሄዱ ያሉት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴዎች መጠናከር አለባቸው ያሉት አቶ ዮሴፍ ተሃድሶው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርበዋል ።
በአገሪቱ እየተገነባ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለቀጣይ የአገሪቱ ልማት ወሳኝ በመሆኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ድጋፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል ።
በመጨረሻም በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኢህአዴግና አጋር ድርጅት ተወካዮች በህወሃት በዓለ ላይ የአጋርነት መግለጫ በማቅረብና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎችን በጋራ ለመታገል ቃል ገብተዋል ።