የግብጽ መንግስት በዓባይ ጉዳይ ላይ መለሳለስ እያሳየ መሆኑ ተመለከተ

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጥበቅ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗ ተገልጿል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በኬንያ ባደረጉት የአንድ ቀን ይፋ ጉብኝታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ከሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በናይሮቢ ከተማ ተገናኝተዋል ፡፡

ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ በዚሁ ጉብኝታቸው አገራቸው በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር ለመተባበር፣ ከአባልነት ራሷን ካገለለችበት የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ጋር ደግሞ በድጋሚ ለመነጋገር የሚያስችል የተለሳለሰ አቋም አሳይተዋል ነው የተባለው፡፡

ግብጽና ኬንያ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት በቀጣናዊ ጉዳዮችና ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋትን መስማማታቸውን መሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

እንደዚሁም የሁለቱ መሪዎች የዓባይ ውኃ ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ መወያየታቸውን ነው የተገጸው ፡፡

በተለይም ፕሬዚዳንት አልሲሲ የውኃ ሀብቱንና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ የኬንያ አቻቸው በተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እገዛ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

ከናይሮቢ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የግብፅ ፕሬዚዳንት የዓባይ ውኃን ፍትሐዊ አጠቃቀምን በተመለከተ ከኬንያው አቻቸው ጋር መነጋገራቸው ታውቋል፡፡

‹‹ኬንያና ግብፅ በዓባይ ውኃ አማካይነት በአንድ የደም ዝውውር የተገናኙ ያህል የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ትስስር ያላቸው አገሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን አጋጣሚ ሁሉ ወደ ተሻለ ልማት ለማሳደግ ድጋፋችንን እናጠናክራለን፡፡ በተፋሰሱ ውስጥ የምንገኝ ሁላችንም አገሮች የእዚህን ታላቅ ወንዝ መልካም በረከቶች ወደ ላቀና የጋራ ተጠቃሚነት ደረጃ ማሳደግ አለብን፤›› በማለት ማሳሰባቸው ተሰምቷል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አባል አገሮችን ከያዘው የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ግብፅ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ራሷን ከአባልነት ማግለሏ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደምነት የተዘጋጀው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በታንዛኒያ በስድስት የተፋሰሱ አገሮች በመፈረሙ ምክንያት፣ ግብፅና ሱዳን ሲያኮርፉ ግብፅ ከኢኒሼቲቩ አባልነት ራሷን ማግለሏ አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግሥት በድጋሚ ወደ አባልነት ለመመለስ ሐሳብ እንዳለው ገልጾ ነበር፡፡

በኬንያ ጉብኝታቸው ፕሬዚዳንት አልሲሲ ይህንኑ ማንፀባረቃቸው ግብፅ ቀደም ብላ ይዛው ከነበረው አቋም መለሳለስ ያሳየችበት ስለመሆኑ ከወደ ናይሮቢ እየተነገረ ነው፡፡

ፕረዚዳንት አል ሲ ሲ የአውሮፓውያን አዲሱ ዓመት ከገባበት ካለፈው ወር ጀምሮ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ጋር ግንኙነት ለማጠናከር አዳዲስ ስምምነቶችን አድርገዋል  ፣

የግብፁ መሪ ከኬንያ ፕሬዚዳንት በመወያየት በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈራርመው ወደ ካይሮ ተመልሰዋል፡፡

አንድ የግብፅ መሪ ኬንያን ሲጎበኝ እ.ኤ.አ ከ1984 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡ የአሁኑ የፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ጉብኝትም ከ33 ዓመታት በኋላ የተካሄደ በመሆኑ በሁለቱም ወገኖች ታሪካዊ ተብሎ ተወድሷል- (ሪፖርተር ጋዜጣ )፡፡