ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች-ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ኢትዮጵያ ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሴናተር ጀምስ ኢሆፍ የተመራ የአሜሪካ የልዑካን ቡድንን ከትናት በስቲያ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ማናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡

የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያሻክር አንዳችም ነገር እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው የአገራቱ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበው የአሜሪካ መንግስት ለአፍሪካ አገራት የሰጠውን ከቀረጥ ነፃ የንግድ ልውውጥ ዕድል (አጎአ) ትኩረት እንዲሰጥም አመልክተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ መሪ ሴናተር ጀምስ ኢሆፍ በበኩላቸው አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ከፈጠረችባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ሴናተሩ ገልፀው በተለይም በቀጣናው ሠላምና ደህንነት ዙሪያ ኢትዮጵያ ትልቅ ሥራ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡ የአገራቱ ግንኙነት በፕሬዚዳንት ሮናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡፡

አዲሱ የኤሜሪካ አስተዳደር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሠላምን ለማስፈን ለምታደርገው ጥረት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሴናተሩ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ አገራት በተለይም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በቅርበትና በትብብር እየሰሩ ሲሆን የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እአአ በ1903 ነው የተጀመረው፡፡