የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ ሴቶች መታገል ይገባቸዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ ሴቶች ሊታገሉ እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  አቶ ኃይማርያም ደሳለኝ ከዋልታ ጋር ባድረጉት ቆይታ ተናገሩ ።

የኢትዮጵያ ሴቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ  እንቅስቃሴዎች እኩል ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ  በማያቋርጥ ሁኔታ ትግል ማካሄድ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ።

የሴቶች ተሳትፎና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መንግሥት የህግ ማዕቀፍ  በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የሴቶች እኩል ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት  ለህብረተሰብ ለውጥ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ  የሴቶችን ትግል ወንዶችም ሊደግፉት ይገባል ብለዋል ።

ሴቶች ያልተሳትፉበት ልማት  በየትኛውም ሁኔታ ውጤታማ  ሊሆን የማይችል በመሆኑ በአገሪቱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሴቶች የሚያድርጉትን ተሳትፎ ማጎልበት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር  ኃይለማርያም ጠቁመዋል ።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች በንግድ ሥራ ፣ በሃብት ፈጠራ፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፎች በመግባት እያስመዘገቡት ያሉት ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶች በሙሉ አቅማቸው በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቡ የሚገቷቸውን እንቅፋቶች ደረጃ በደረጃ በመለየት መፍትሄ መሥጠት ይገባል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ  ሴቶች  አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት መንግሥት ለመጣል በተካሄደው እልህ አስጨራሽ  ትግል ከማጀት  ጀምሮ  በትጥቅ ትግሉ  በመሳተፍ በአገሪቱ  ታላቅ  ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ የበኩላችውን ድርሻ መወጣታቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም አስረድተዋል ።

ሴቶች በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደት ላይ  ባለፉት  25 ዓመታት  የነበራቸውም ተሳትፎ  ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ  በአገሪቱ  በተካሄዱት ተከታታይ አገራዊ  ምርጫዎች ላይ ተወካዮቻቸውን በመምረጥና በተለያዩ አደረጃጃቶች ንቁ ተሳትፎ  በማድረግ  ዴሞክራሲ  እንዲያብብ  ጉልህ ከፍተኛ  ሚና ተጫውተዋል ።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ አሁንም ድረስ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱት ኋላ ቀር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሆኑት የሴቶች ግርዛት ፣ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈርና የሴቶች ትንኮሳ አለመቅረታቸውንና ድርጊቶቹን ለመከላከል ይበልጥ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ።

በአገሪቱ  በውሳኔ  ሰጪ መድረኮች ላይ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንና  በታችኞቹ ምክር ቤቶች  የሴቶች ተሳትፎ  ከ 50 በላይ መድረሱን እንዲሁም  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ 38  በመቶ መሆኑ  አበረታች መሆኑን  ጠቅላይ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል ።

በአሁኑ  ወቅትም  በአገሪቱ  የሴቶች  የትምህርት ተሳትፎ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች   ከወንዶች እኩል ፣ በሁለተኛ ደረጃ ከ 50 በመቶ በላይ መሆኑንና  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  የሴቶች ተሳትፎ  ከ40  በመቶ በላይ መድረሱ ትልቅ እመርታ መሆኑን ጠቅላይ ሚንሰትሩ አያይዘው ገልጸዋል ።

ለ41ኛ ጊዜ  የሚከበረው ማርች አይት በዓል “ ህዳሴያችንን ለማረጋጋጥ  ሴቶች በቁጠባ  ላይ የጀመሩትን  ሥራ አጎልብተው  መቀጠል አለባቸው ”  በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  ዘግቧል ።