የታላቁ ህዳሴ ግድብን እውን ለማድረግ የሴቶች ሚና ቁልፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናገሩ

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ( ማርች 8) ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት  በግንባታ ላይ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን  በተያዘለት የጊዜ  ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የሴቶች የድጋፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል ።

ትናንት በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ 2ሺ 500 ተወካይ ሴቶችን  ባወያዩበት ወቅት አቶ ኃይለማርያም እንደገለጹት ማርች 8 ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች መራራ ትግል በማድረግ በሚደርሱባቸው የተለያዩ  ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናዎች ላይ ድል መቀናጀታቸውን  የሚያስታውስ ቀን ነው ብለዋል ።

ሴቶች ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ  መከበር  ከባድ መስዋትነት በመክፈል  ጭቆናን ለማስወገድ  ታሪካዊ   ትግል ማካሄዳቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች ከቀደሙት ሴቶች በተለየ ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው  መሠረት ጥቅሞቻቸውና  መብቶቻቸው በመከበራቸው ምክንያት   በአገሪቱ  በተመዘገቡት የፖለቲካዊና  ማህበራዊ ለውጦች  ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።

ሴቶች ከመንግሥት  ድጋፍ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ይበልጥ በማስከበር በራሳቸው  ብርቱ እንቅስቃሴ በማድረግ  ለአገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ዕድገት  አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ  ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል ።  

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ የሴቶችን  ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ የሴቶች የቁጠባ ባህልን ከማሳደጉም  በላይ  ለአገር ኢኮኖሚ  ገንቢ ሚና ይጫወታል ።

በትናንትናው  ዕለት  በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የተካሄደው ውይይት  ከተጠናቀቀ በኋላ  ባለፉት ሦስት  ወራት በቁጠባ የተሻለ አፈጻጻም ያስመዘገቡ ሴቶች  ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሽልማት ተበክቶላቸዋል ።

በመጨረሻም  ተወካይ ሴቶቹ  ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም  የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ ተሠጥቷቸዋል ።

የዘንድሮ 41ኛው  ዓለም አቀፍ የሴቶች  ቀን “ህዳሴያችንን ለማረጋጋጥ  ሴቶች በቁጠባ  ላይ የጀመሩትን  ሥራ አጎልብተው  መቀጠል አለባቸው ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል ።