የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣2ኛ ዓመት የስራ ዘመን ፣6ኛ መደበኛ ጉባኤ ከሰኞ ጀምሮ እንደሚያካሄድ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አፈ ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ 5ኛዉ መደበኛ ጉባኤው በ6 ወራት አፈጻጸም ግምገማ ላይ በማተኮር ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 7/2009 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በዋናነትም የአስፈጻሚ አካላት የተጠቃለለ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅድ፣የክልሉ የዳኝነት አካላት የዕቅድ አፈጻጻምና የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ እንደሚገመገም አመልክተዋል፡፡
አቶ ይርሳው አክለውም ጉባኤው የክልሉ መንግስት በየዘርፉ የተፈጸሙ ተግባራትን የሚገመግም ቋሚ ኮሚቴ አቋቁሞ ክትትል ሲያደርግ እንደቆየና የነበረው አፈጻጸምም በምክር ቤቱ ቀርቦ እንደሚገመገም ገልጸው ከዚህ በተጨማሪም የምክር ቤት አባላት የህዝብ ወኪሎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የህዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ካለፉት ዓመታት በተሻለ መንገድ የመረጣቸውን ህዝብ በቀጥታ እንዲያገኙ በማድረግ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የተሰሩ ስራዎችም በምክር ቤቱ እንደሚገመገሙ አቶ ይርሳው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለልማት፣መልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጋዥ የሆኑ የተለያዩ አዋጆች እንደሚጸድቁ የገለጹት አቶ ይርሳው ምክር ቤቱ ልዩ ልዩ ሾመቶችንም እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡