የሽብር ተግባር ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ 16 የኦነግ አባላት በእስራት ተቀጡ

የአሸባሪው ኦነግ አባል በመሆን የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ውለው ከተከሰሱ 21 ግለሰቦች መካከል 16ቱ ላይ ከአራት እስከ 13 አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ቅጣት ተወሰነባቸው ።

ከ21ዱ ተከሳሾች መካከል 1ኛ ኦላና ከበደ፣ 2ኛ ወልዴ ሞቱማ፣ 3ኛ አርገም ሲሳን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ ነው ዛሬ ቅጣቱ የተላለፈው።

ተከሳሾቹ እድሜያቸው ከ18 እስከ 49 የሚደርሱና አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች ናቸው።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ በሃይል የሃገሪቱን ህዝቦች አንድነት የማፈራረስ እና የኦሮሚያ ክልልን ከፌዴሬሽኑ የመገንጠል አላማን ይዘው ተንቀሳቅሰዋል።

በዚህም የሃገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገ መንግስታዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ ከሚንቀሳቀሰው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ብሎ በሚጠራው ሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ አባል ሆነው መንቀሳቀሳቸውም ተጠቅሷል።

ራሳቸውን በህዋስ በማደራጀትና የስራ ክፍፍል በማድረግም፤ ሌሎች አባላትን በመመልመል ምዕራብ ሸዋ ዞን አድአ በርጋ ወረዳ ኦሎን ኮሚ አካባቢ በሚገኘው በሩዴ ጫካ ውስጥ ለሚገኘው የሽብር ድርጅት ታጣቂዎች የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ማድረጋቸውም በክሱ ተዘርዝሯል።

ቀድሞ ከእነርሱ ጋር ይተባበር የነበረ ግለሰብ እና የሽብር ድርጅቱ እንቅስቃሴ የተሳሳተ ነው በማለት ከመንግስት ጋር ይሰራል የሚሉትን ግለሰብ ለመግደል ተልዕኮ መቀበላቸውንም ክሱ ያስረዳል።

በውጭ ከሚገኘው የሽብር ድርጅቱ ገንዘብ በመቀበልም፥ ግለሰቡ የሚኖርበትን ቤት በማጥናት ለመግደል በተደጋጋሚ ወደሚኖርበት ቤት ተንቀሳቅሰው ተልእኳቸውን መፈጸም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉ ተከሳሾች አላማቸውን ለማሳካት በበሩዴ ጫካ ውስጥ በመግባት የሽብር ድርጊቱን በተደራጀ መልኩ ለመፈፀም ምርጫ አካሂደዋል።

በዚህም የቡድን ሃላፊ፣ ገንዘብ ያዥ፣ ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀ መንበር በመምረጥ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሚገኘው 6ኛ ተከሳሽ አብዲሳ ኢፋ ሪፖርት አድርዋል።

በዚሁ ወር ጃለታ ለሚ ለተባለ የኦነግ ሽብር ቡድን አባል ስልክ በመደወልም የ2007 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ሲገለጽ፤ ምርጫው ተጭበርብሯል ብለን ህዝቡን ለማሳመጽ ቅስቀሳ እናደርጋለን የሚል ተልዕኮ በመቀበል መንቀሳቀሳቸውም በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹ የተለያዩ የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶችም በእጃቸው ተገኝቷል።

ወደ ኬንያ በመሄድም በተለያዩ አካባቢዎች ከሽብር ድርጅቱ አመራሮች ጋር በመገናኘት የተለያዩ ስልጠናዎች መውሰዳቸውን አቃቢ ህግ በመዝገቡ ጠቅሷል።

በአጠቃላይ አቃቢ ህግ በ21ዱ ተከሳሾች ላይ በተናጠልና በቡድን አራት ከሽብር ወንጀል ጋር የተያያዙ ክሶችን መስርቶባቸዋል።

የግራ ቀኙን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎትም፥ ከ21ዱ ተከሳሾች መካከል 16ቱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽን በ13 አመት ጽኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽን በ12 አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ፥ 4ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 10ኛ፣17ኛ እና 19ኛ ተከሳሾችን በአራት አመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት እንዲሁም 7ኛ እና 18ኛ ተከሳሾችን ደግሞ በአራት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

መከላከያ ምስክር አቅርበው ያልጨረሱት 3ኛ፣ 5ኛ፣ 20ኛ እና 21ኛ ተከሳሾች ደግሞ መከላከያ ምስክር ማሰማታቸውን ቀጥለዋል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።