መድረኩ በህዝብ፣በድርጅቱና በፈጻሚ አካላት መተማመንን የፈጠረ ነው -ህወሓት

 

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ የተካሄዱት መድረኮች በህዝብ፣በድርጅቱና በስራ ፈጻሚ አካላት መተማመንን የፈጠረ መሆኑን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ ፡፡

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሶስት ቀናት በመቐለ ከተማ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባው ሲያካሂድ ፤በልማታዊ ሰራዊት ቅኝት የተካሄዱ ጥልቅ ተሃድሶዎች ባለፉት  ዓመታት የተገኙ ድሎችና ክፍተቶች መሰረት አድርገው በትግራይ ህዝብ ፣በመሪ ድርጅቱና በስራ ፈጻሚ አካላት መካከል መተማመን የፈጠሩ መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

በተለይም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስርዓት አደጋ ናቸው ተብለው አስቀድሞ የተለዩት ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባራት፣ጸረ- ዲሞክራሲ፣ጠባብነት፣ትምክህትና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በጥልቀት ገምግሟል ፡፡

ይህም መድረኩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ህዝቡ የተጋጋለና የተቀናጀ ትግል በመፍጠር ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር የተሻለ ዕድል የፈጠረ መሆኑን መግለጫው አስረድቷል ፡፡

ጥልቅ ተሃድሶው በፈጠረው ምቹ ሁኔታም ባለፉት ስድስት ወራት የላቀ ዓቅም የተፈጠረባቸው የመልካም አስተዳደር ድሎች መመዝገባቸውን አስታውቋል ፡፡

በገጠር የእርሻና የመስኖ ስራዎች፤ በከተሞችም በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋሞች የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች በአብነት አንስቷል ፡፡

የተጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ቀጣይነት ያለው የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያለው ፡፡

የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ለመመለስ በድርጅቱ ውስጥ፣በመንግስትና በህዝባዊ ማህበራት ተቋማዊ ዓቅም ግንባታ ሊጠናከር እንደሚገባም አስገንዝቧል ፡፡

ይህም ተጠያቂነትን በማስፈን በውጤት የሚለካ ስራ ለመስራት ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጡን አመልክቷል ፡፡

ኪራይ ሰብሰቢነትን፣ጠባብነትና ትምክህትን በመታገል ከእህት ድርጅቶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር አሁንም የማያቋርጥ ትግልና መድረኮች እንደሚያስፈልጉ ገልጿል ሲል የዘገበው ድምጺ ወያነ ሓርነት ትግራይ ነው ፡፡