ኢህአዴግና አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ አጀንዳዎቻቸው ያለአደራዳሪ አካል ለመወያየትና ለመደራደር መወሰናቸውን አስታወቁ ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ በተካሄደው 7ኛው ዙር ድርድር ላይ የኢህአዴግና ሌሎች 13 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥር 10/2009 ዓመተ ምህረት ያቀረቡዋቸውን የመደራደሪያና የመወያያ አጀንዳዎቻቸው ያለማንም ገለልተኛ አደራዳሪ አካል ድርድር የሚመሩበት ደንብ ለማጽደቅ ወስነዋል ፡፡
ኢህአዴግ በሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም ሊይዝና የሚችልና ነጻ ሊሆን ስለማይችል ያለአደራዳሪ ሊሆን ይገባል የሚል ሃሳቡን አቅርቧል ፡፡
እንደ ኢህአዴግ አቋም ድርድሩ በሁለትዮሽ ፣የተለየ አጀንዳ ያለው ፓርቲም ካለ በግል ያለ አደራዳሪ ፤ካልሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመረጧቸው ተወካዮች በዙር ለማካሄድ መወሰኑን ነው ደግሞ ያስታወቀው ፡፡
ይህንን ሃሳብ ከሞላ ጎደል መየደገፉት አንድነት፣ ቅንጅት፣ አትፓ፣ ኢዴአን፣ ኢዴህ፣ ወህዴፓ፣ ኢዴአንና ገዳ ይገኙባቸዋል ።
እነዚህ ፓርቲዎች ቀጣይ ክርክራቸውና ድርድራቸው በዙር ይሁን በሚል ይዘው የቀረቡትን ሃሳብ ዛሬም ደግመው አንጸባርቀዋል ፡፡
አዴፓ፣ መኢአድ ፣ሰማያዊ ፓርቲ ፣ኢብኢን፣መኢዴፓ እና ኢራፓ ግን ያለአደራዳሪ አጀንዳዎቻቸው ላይ ለመወያየት አንፈልግም የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል ፡፡
ይሁንና አዴፓና መኢአድ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ዕድል እንዲሰጣቸው በመጠየቅ “እዚህ ያለነው ሰዎች ጨርሰን መወሰን አንችልም ፤ስለሆነም በቀጣይ ሳምንት የፓርቲዎቻችንን ስራ አስፈጻሚ አካላትና መላ አባላቶቻችን ጋር መክረንና ተወያይተን ያለአደራዳሪ እንቀጥላለን ወይስ አንቀጥልም የሚለውን መጥተን እንሳውቃለን” ብለዋል ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ግን “በዓለም ላይ ያለአደራዳሪ የሚካሄድ ድርድር ስለሌለ መደራደር አንፈልግም!” ሲሉ አረጋግጠዋል ፡፡
እንዲያውም ሊቀመንበሩ “ያለአደራዳሪ የሚደረገውን ውይይት የገፋው ኢህአዴግ ስለሆነ አንቀበለውም፤ ያለአደራዳሪ የሚቀጥል ከሆነ ግን ተመልሰን ልንወያይ እንችላለን” የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል ፡፡
በመጨረሻም ኢህአዴግ ያለአደራዳሪ ለመወያየትና ለመከራከር የወሰኑትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ ለመቀጠል ያረጋገጠ ሲሆን ምናልባት ያለ ሶስተኛ ወገን እንደራደርም ያሉ ፓርቲዎች ዕድሉ ሊጠቀሙበት ከፈለጉ በሩ ክፍት መሆኑን አስታውቋል ፡፡
ኢህአዴግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የዲሞክራሲ ባህሉን ለማጎልበት በሚል ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአገር ጉዳይ ላይ ለመወያየትና ለመደራደር መወሰኑን አስታውሷል ፡፡
በቀጣይ ሀሳባቸውን የቀየሩ ተቀዋሚ ፓርቲዎች ካሉ ለመቀበልና የድርድር ደንቡን ተወያይተው ለማጽደቅ ሚያዝያ 2/2009 ዓመተ ምህረት በመወሰን የዛሬ ስብሰባቸው ማጠናቀቃቸውን ዋልታ ዘግቧል ፡፡
በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው መድረክ ግን በዚሁ ድርድር ስብሰባ አለመገኘቱን ለማረጋገጥ ተችሏል ፡፡