አፍሪካውያን ከዛምቢያ ዴሞክራሲ ሊማሩ ገባል-ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ

አፍሪካ ከዛምቢያ የዴሞክራሲ ስርዓት ትምህርት ልትወስድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

የዛምቢያ ቋሚ የጋራ ኮሚሽን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በሉሳካ ዛምቢያ መክሯል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ በአምስት የፕሬዝዳንት ዘመን የተከወኑ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሮች የዛምቢያ ዴሞክራሲ ማደጉን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ህዝቦች ለሚያስተዳድሯቸው መሪዎች የሚያሳዮት ክብርንም አድንቀዋል ፡፡   

ኢትዮጵያና ዛምቢያ የኢኮኖሚ ተግዳሮታቸውን ለመቅረፍ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው፡፡

እየጨመረ የመጣው ሚዛናዊ ያልሆነ የንግድ ምጣኔ፣ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ፣ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገት ማሽቆልቆል እና የአየር ንብረት ለውጥን የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ተዳምረው ጥቂት የሚባሉ ውጪያዊ ውስንነቶች ለሁለቱ ሀገሮች የኢኮኖሚ ችግሮች መከሰት አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡       

የዛምቢያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሀሪ ካላባ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት እንደምትፈርም ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ ሀገሮች ባቋቋሙት የጋራ ኮሚሽን ለተላለፉ ውሳኔዎችና አፈፃፀማቸው ቁርጠኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ካላባ አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡