“ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገሮች ነጻነት መጎናጸፍ ታላቅ ሚና ነበራት” ሲሉ የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ገለጹ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም “የአሁኑ ትውልድ መሪዎች የእናንተን ፈለግ በመከተል በአህጉሪቷ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት ለማምጣት እንሰራለን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት ከአፍሪካ የነጻነት ታጋይ ከ92 ዓመቱ ኬኔት ካውንዳ ጋር ሉሳካ ውሰጥ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የዛምቢያ መሪ ካውንዳ በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበራትን የመሪነት ሚናን በማስታወስ “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነትና ዕድገት የላቀ ሚና ተጫውታለች” ሲሉ አድንቀዋል።
ዛምቢያና ኢትዮጵያ መልካም የሆነ የመንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ግንኙነቱ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ እስካሁን የዘለቀ መሆኑንም አውስተዋል።
“አገሪቷ ነጻነቷን ለመጎናጸፍ ላደረገችው ጥረትም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ድጋፍ ጉልበት ሆኖናል” ሲሉም ነው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ የገለጹት።
የጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዛምቢያ ጉብኝትም "የሁለቱ አገሮች ጠንካራ ግንኙነት የመቀጠሉ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዛምቢያ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የነጻነት ትግል ሰኬታማነት ጉልህ ሚና እንደነበራት ያስታወሱት የቀድሞው የዛምቢያ መሪ ካውንዳ፤ "በትክክልም የአፍሪካ ማዕከል መሆን ያለባት አገር ናት" ሲሉም አወድሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ህብረት በኩል አገሪቷ እያከናወነች ያለውን ተግባር ኬኔት ካውንዳ አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ፤“የሶስተኛው ትውልድ መሪ ሆኜ ከእርስዎ ጋር ባደረግሁት ቆይታ ደስታ ተሰምቶኛል” ነው የገለጹት ፡፡
“እናንተ ታግላችሁ የፖለቲካ ነጻነት አስገኝታችኋልና፤ እኛም የኢኮኖሚ ነጻነት ለማምጣት እንሰራለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያና ዛምቢያ በቀጣናዎቻቸው ያለውን አለመረጋጋት ለማስወገድ የታላላቆችን የፓን አፍሪካኒዝም ተሞክሮ በመውሰድ "ለአካባቢያችን ሰላም በጋራ እንሰራለን " ነው ያረጋገጡት ።
በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ውህደት ለማምጣት የአሁኑ ትውልድ መሪዎች የእናንተን ፈለግ በመከተል ትግሉን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛምቢያን በማገልገል ያለፉ የሶስት ፕሬዝዳንቶች የመታሰቢያ ኃውልትን በመጎብኘት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛ፣ ሶስተኛና አምስተኛ የአገሪቷ ፕሬዝዳንቶች ፍሬዴሪክ ችሉባ፣ ሌቪ ፓትሪክ ምዋናዋሳ እና ሚካኤል ቺሉፊያ ሳታ የመታሰቢያ ኃውልት ስር ነው የአበባ ጉንጉን ያኖሩት።
በዚህ ወቅትም የአገሪቷ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ዛምቢያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1964 አንስቶ የአገሪቷ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት በመሆን ለ27 ዓመታት ያገለገሉ ታላቅ መሪ ናቸው – ኬኔት ዴቪድ ካውንዳ-(ኢዜአ )።