በሀገሪቱ ለተመዘገቡት ሁለንተናዊ ለውጦች ዋልታ ሲያበረክት የነበረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር ፡፡

በሀገሪቱ ለተመዘገቡት ሁለንተናዊ ለውጦች ዋልታ ሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሲያበረክት የነበረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የዋልታ ቴሌቪዥን ዛሬ መጀመሩን አስመልክተው ከጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ ዋልታ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ሙስና እንዲቀንስ በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል ፡፡

በእስካሁኑ ሂደት የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች በከባድ የሥራ ሂደቶች ተፈትነው የወጡ በመሆናቸው ስኬታማ ስራ ማከናወን እንደሚያስችላቸው ነው የገለጹት ፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ካለው የቴሌቪዥን መስፋፋት ጋር ተያይዞ ዋልታ በሁሉም መሰፈርት ቢመዘን ከማንም በላይ የሆነ ዓቅም ይዞ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ዋልታን በቦርድ የመሩበት ጊዜ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ያኔም የራሱ ቴሌቪዥን ይኖረው ዘንድ ብዙ ስራዎች ሲያከናወን እንደነበር አስታውሰዋል ፡፡

በዶክመንተሪ ስራዎቹም ብቻ ሳይሆን የሚሰራባቸው የጥራት ደረጃዎች ዓለም አቀፍ ደረጃ ነበራቸውም ነው ያሉት፡፡

ዋልታ የህዝብን ሀሳብ ታች ድረስ እንዲደርስና ይህንን ሀሳብ በጥናት ላይ ተመርኩዞ በማቅረብም ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ ነው ሲሉ አስታውቀዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ኢትዮጵያን በማሰተዋወቅ ረገድ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲሰራ መቆየቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲያገኝ አድርጎታል ባይም ናቸው ፡፡

ዋልታ ከምስረታው ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ባህልና እሴቶች ከማስተዋወቅ ባሻገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ እነዚህን እሴቶቸ እንዲጋሩ አድርጓልም ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ሲኤን ኤን እና ቢቢሲን የመሳሰሉት ተቋማት ጋር በመስራት እንደ ሀገር ያበረከተው አስተዋጸኦ ግንባር ቀደም እንደሚያደርገው ገልጸዋል ፡፡

እነዚህ ሲደመሩና ያሉት የድምፅና የምስል ክምችቶች ሲታሰቡ ለቴሌቪዥን ከማንም በላይ ጥልቅ አቅም ይዞ ወደ ውድድር ሜዳው እንዲገባ እንዳደረገውም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባስመዘገበችውና አሁንም በቀጠለው ሀገራዊ እድገትም ውስጥም የዋልታ ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ዋልታ ለዚህ ስኬቱ ደግሞ ብቃቱ ልምዱና ተነሳሽነቱ ያላቸው ሰራተኞችን ይዞ መስራቱም ከፍ ያለ አቅም እንደፈጠረለት አስረድተዋል ፡፡

በብዙ ችግሮች የተፈተኑ አመራሮች ያሉትና እነዚህ አመራሮችም እስካሁን አብረው መዝለቃቸው ለስኬቱ በአብነት የሚጠቀስና ሌላ ቦታ የሌለ ሀብት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ፡፡

በሀገሪቱ አሁን ያለው የመድበለ ፓርቲ እንቅስቃሴ እንዲዳብር፤ የመልካም አስተዳደር ስራ እንዲጠናከር፤ ኪራይ ሰባሰቢነት እንዲከስምና የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲጠናከር የበለጠ መስራት ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የዋልታ ቴሌቪዥን እውን ይሆን ዘንድ ሲታትሩና ሲለፉ ለቆዩት አመራሮችና ሰራተኞቹ እንዲሁም አማራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሆኖ ለመጣለት የኢትዮጵ ያህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

አርታኢ -በሪሁ ሽፈራው