የመገናኛ  ብዙኃን የህግ የበላይነትንና የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ

የመገናኛ  ብዙሃኑ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካል ጋር በመሆን  የህዝቦች አንድነት፣ የህግ የበላይነትን፣ የሃሳብ ብዝሃነትን፣ ማስተናገድ እና የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ ፡፡

“የሚዲያ ሚና በኢትዮጵያ፣ ፈተናዎችና ዕድሎች” በሚል ርእስ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ከፓነል ተሳታፊዎቹ ውስጥ ሚዲያ የክርክር መድረክ ሆኖ በማገልገል እንዲሁም ስህተቶችን ነቅሶ በማውጣት በሀገሪቱ መስረታዊ የሚዲያ ህጎች ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ አሁን ያለውን ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት መሙላት እንዳለበት በፌደራል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኢታ አቶዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል ፡፡

በሀገሪቱ መስረታዊ የሚዲያ ህጎች ማእቀፍ ውስጥ መሰረታዊው ጉዳይ ህዝብን ከድህነት ማላቀቅ በሆነበት ሀገር የመገናኛ  ብዙሃኑ ከመንግስት ጋር ባለድርሻ አካል በመሆን  የህዝቦች አንድነት፣ የህግ የበላይነትና የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ እንዲሁም የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስተዋወቅም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ፡፡

ወቅታዊ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለህዝብ በማድረስ ሚናውን መወጣት አለበት ያሉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ ናቸው፡፡

የመገናኛ ብዙሃኑ ከሚያካሂዱት ውይይትና ክርክር ህዝብና ሀገር ጠቃሚ ሃሳብ የማግኘት መብት እንዳላቸው በመገንዘብ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብንና ተግባራት ለማጋለጥ መስራት እንደሚያስፈልግም የዋልታ ሚድያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተተካ በቀለ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እስካሁን ያከናወኑት ተግባሮች ቢኖሩም ወደሚፈለገው ግብ ከመድረሱ አንፃር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ደግሞ የኦሮምያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ወየሳ ገልጸዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው በግሉም ሆነ በፐብሊኩ የመገናኛ ብዙሃን የሚታየው ዋናው ፈተና የአቅም እና የአመለካከት ሆኖ የመሰረተ ልማት ችግርም ተጠቃሽ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

የሚዲያ አመራሩ ራሱም ሃላፊነት ወስዶ የመስራት ችግር እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡

በመንግስት በኩልም የሚዲያ ተቋማትን በእኩል ዓይን ያለማየት ችግር መኖሩንና መንግስት ለሚዲያ ቅርብ አለመሆኑም የገለፁት ደግሞ የዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽንስ ምክትል ዋና ስራአስፈፃሚ ወይዘሮ ሚሚ ስብሃቱ ናቸው ፡፡

መንግስትና ሚዲያዎች የጋራ ጉዳይ እያላቸው መረጃ ከመስጠት ጀምሮ በሚዲያ ስራ ዙሪያ ለተሰማሩ በማስታወቂያ አቅርቦትና በሌላ መልክ የመንግስት ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ተጽእኖ ፈጣሪ ሚዲያ መፍጠር አልተቻለምም ብለዋል ተሳታፊዎቹ ፡፡

መንግስት በሚዲያ መሳሪያዎች የጣለው ከፍተኛ ታክስም ተጽእኖ እንዳሰደረባቸውም አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡

እናም ሀገሪቱ በልማት ከተጓዘችበት አንፃር ሲታይ ሚዲያዎች የግማሹን ያህል ስኬት አላስመዘገቡም ነው ያሉት ፡፡

የካበተ ልምድና አቅም ያለው የሚዲያ አመራር እጥረት እንዲሁም በእውቀት ታግዞ ነገሮችን መደገፍና መቃወም ላይም የሚዲያዎች እጥረት ነው ብሏል፡፡

ከዚህ በተለይም ሚዲያው የተገለፁ ሃሳቦችና የተደረጉ ድርጊቶችን ከማስተላለፍ አንፃር ራሱን በማቀብ ለሚተላለፉ ይዘቶች መዳከም ሃላፊነት መወሰድ እንዳለበትም ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች ያስገነዘቡት ፡፡

የሚዲያ ተቋማት የሰው ሃይል ልማት በማካሄድ ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀት አለብን ያሉ ሲሆን መንግስትም ለመረጃ እና ለድጋፍ ቅርብ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የሚመለከታቸው አካላትም በቅርቡ አሳታፊ የሆነ የሚዲያ ሪፎርም ፕሮግራም እንደሚቀረጽ መግለፃቸውን ዋልታ ዘግቧል፡፡ 

አርታኢ -በሪሁ ሽፈራው