የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋርም በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዲፕሎማሲው መሰክ እየሰራች ነው ብለዋል።
ሃገራቱን በባቡር ትራንስፖርት ለማስተሳሰር ጥናት ተደርጎ መጠናቀቁን ጠቅሰው፥ በቅርቡ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
ሃገራቱ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጋራና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም በቀጠናው ያለውን ቀውስ ለመፍታት በተለይም አል ሸባብን ለመደምሰስ በጋራ እንደሚሰሩም አንስተዋል።
ሁለቱ ሃገራት ነጻ የኢኮኖሚ ቀጠና ለመፍጠር የሚያስችላቸውን አሰራር ለመተግበር እየተንቀሳቀሱም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል በሽር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ የህዝብ ለህዝብ ቁርኝት ያላቸውና በባህል የተሳሰሩ ጎረቤታሞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሃገራቸው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር፥ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በፀጥታና ደህንነትን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች በጋራ እየሰራች መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የመንገድ ዝርጋታ፣ መሰረተ ልማት፣ በቴሌኮምና ሌሎች መሰረት ልማቶች ሃገራቱ መተሳሰራቸውንም ነው የገለጹት።
ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ በመፍጠርም አፍሪካ ለምታደርገው የኢኮኖሚ ውህደት ሞዴል ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውንም በውይይቱ ወቅት ጠቁመዋል።
መሪዎቹ በውይይታቸው ሃገራቱ በተፈራረሟቸው የመግባቢያ ስምምነቶች አተገባበር ዙሪያም መክረዋል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።