ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያና ሱዳን የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ጥረት ለቀጠናው አገራት አብነት ሊሆን እንደሚችል ገለጹ።
የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ትናንት በኢትዮጵያ ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ዙሪያ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያና ሱዳን በመካከላቸው የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር እያደረጉት ያለውን ጥረት ለቀጠናው አገራት አብነት ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አገራቱ በኢኮኖሚ ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ሱዳን ድረስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን አስታውሰዋል።
ከኢትዮጵያ ሱዳን ወደብ ድረስ የባቡር መሰረተ ልማት ለመዘርጋት አስፈላጊው ጥናት መካሄዱንና በሚቀጥሉት ወራት ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ወደብ መጠቀም መጀመሯንና በተያዘው ዓመትም ወደቡን በመጠቀም ማዳበሪያ ማስገባቷን ነው የገለፁት ።
አገራቱ በኤሌክትሪክ ሃይል መተሳሰራቸውም ለኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
የአገራቱን የረጅም ዓመታት ወዳጅነት በኢኮኖሚው ዘርፍ የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱንና ለሌሎች አገራት ምሳሌ እንደሚሆን ነው አቶ ሃይለማርያም ያስረዱት ።
''በሱዳንና በኢትዮጵያ የሚከሰተው ማንኛውም የጸጥታ ችግር የኛም ችግር በመሆኑ በደህንነትና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሰራለን'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
አያይዘውም ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሶማሊያን ከአልሸባብ ለመከላከልና መልሶ ለማቋቋም ከኢጋድ አባል አገራት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ነው የገለፁት።
በቅርቡ ወደ ካርቱም በመሄድ ተመሳሳይ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ቤንዚል ማስገባቷና ሱዳንም ከኢትዮጵያ 300 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀሟ የኢኮኖሚ ትስስሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
በደህንነትና ጸጥታ ጉዳዮች የገቧቸው ስምምነቶችም ተግባራዊ መደረጋቸውን ፕሬዚዳንት አልበሽር አረጋግጠዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ሶስቱ አገራት የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።