በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳድር በቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት የደረሰዉን የእሳት አደጋ በተመለከተ የተካሄደዉን ምርመራ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፍትህ እና አሰተዳደር ጉዳዮች ቆሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ቃጠሎው ሆነ ተብሎ እንዲነሳ መደረጉን ነው የገለጸው።
የእሳት አደጋው እንዲነሳ ያደረጉት በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው የፍርድ ሂደቱን የሚጠባበቁ እስረኞች መሆናቸውን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገዉ ምርመራ የአደጋዉን መነሻ፣ የደረሰዉን የአደጋ ዝርዝር እና ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ጭምር የያዘ ነዉ ።
ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገዉ ምርመራ እንዳመላከተዉ የ23 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ቀላል እና ከባድ ጉዳት መደረሱን እንዲሁም የ15 ሚሊየን ብር ንብረት መዉደሙን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
21 እስረኞች በጭስ ታፍነው መሞታቸውን እና ሁለቱ ድግሞ ሊያመልጡ ሲሉ በተተኮሰባቸው ጥይት መሞታቸውን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በሰጠው አስተያየት አደጋውን ቀድሞ ማስቆም ይቻል እንደነበር ነው ያመለከተው።
ከአደጋው በፊት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ግሩም ሩምታ እና ረብሻ ተፈጥሮ እንደነበር የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በእስር ቤቱ መግባት የሌለባቸው አደንዛዥ እዖችን ጨምሮ ላይተር እና ለቃጠሎ የሚዳረጉ ቁሳቁሶች መታየታቸውን አመላክቷል።
ኮሚሽኑ በቀረበው ሪፖርቱ ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎች በህግ እንደሚጠየቁ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በእስር ቤቱ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ድርጊቶች እና የእስረኞች አያያዝ መኖራቸውን እንደማሳያ በመጥቀስ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰድ አሳስቧል።
በሪፖርቱም እንደገለጸው የህግ ታራሚዎችን በወንጀል ደረጃ እና እድሜ በመለየት እንዲሁም በማረሚያ ቤቱ የሚታየውን ትፍግፍግ ሁኔታ ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር ታይቶ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት አስገንዝቧል ።
ኮሚሽኑ በቀጣይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝር ሪፖርቱን አቅርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።