“የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለአገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ አድርጓል” – ፕሬዝዳንት አልበሽር

 "በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ ለአገሪቱ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል" አሉ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር።

ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በመሆን በደቡብ ክልል የሚገኘውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ያለው ስላም እየተከናወነ የሚገኘው ልማት እንዲፋጠን የቡኩሉን ድርሻ አብርክቷል።

በተለይም የተመዘገበው ልማት በአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን ማረጋገጫ እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲከታተሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ሰፊ የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ልማቱም በዜጎች ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣቱን ታዝቤያለሁ ብለዋል።

''የኢንዱስትሪ ፓርኩን መጎብኘቴ ደስ አሰኝቶኛል፤ ፓርኩም ለሰለጠነ የሰው ኃይል መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑን ታዝቤያለሁ'' ብለዋል።

''ያየነው ነገር ምሳሌ የሚሆን ነገር በመሆኑ ሱዳን ይህንን ተሞክሮ ወስዳ ትጠቀምበታለች'' ብለዋል ፕሬዝዳንት አልበሽር።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ መላክ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን ምርቱ ለውጪ ገበያ ብቻ የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ እስካሁን ለስድስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን ኩባንያዎቹ በፍጥነት ወደ ስራ እየገቡ በመሆኑ የስራ ዕድሉም በዛው መጠን ይጨምራል ነው ያሉት።

እስካሁን ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከስሪላንካ፣ ከቤልጂየምና ከፈረንሳይ የመጡ 16 ታዋቂ ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ አምራቾች በፓርኩ ገብተዋል-(ኢዜአ) ።