የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄና ሌሎች የልማት ስራ አፈጻጸምን እንደሚገመግም የግንባሩ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ ፡፡
ኢህኤግ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የሁለተኛ ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ዛሬ መጀመሩን የግንባሩ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ስታውቋል ።
ምክር ቤቱ ኢህአዴግ በይፋ የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በአመራሩ፣ በአባል፣ በሠራተኛውና በመላው ህዝብ እንዲታይ የተቀመጠው አቅጣጫ የደረሰበትን ደረጃ እንደሚገመግም ይጠበቃል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ወኪል የሆኑት ትምክህትና ጠባብነት፣ ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል አመለካከትና ተግባራት ድርጅቱንና አገራዊ የህዳሴ ጉዞውን የሚፈታተኑ አደጋዎች መሆናቸውን ጽሕፈት ቤቱ ጠቅሷል ።
በተለይም ህዝብን ጨምሮ በየደረጃው ትግል እንዲደረግባቸው የተቀመጡ የጥልቅ ተሃድሶ አቅጣጫዎች ምን ላይ እንደደረሱ ምክር ቤቱ በዝርዝር እንደሚገመግም ነው ያመለከተው ።
ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባው በየደረጃው ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ እና ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩ ጉዳዮችን አፈፃፀም ይመለከታልም ነው ያለው ፡፡
ግንባሩ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም የማክሮ ኢኮኖሚ፣ በኢኮኖሚና ማሕበራዊ ዘርፍ የተቀመጡ እቅዶች አፈጻጸም እንደሚገመግም ጠቁሟል ።
በመድረኩ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አፈፃፀሞችን በመፈተሽ ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡
ምክር ቤቱ በአገራችን ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት የሰው ህይወት ሳይጠፋና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በራስ ዓቅም ለመቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከት ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው ገልጿል ።