በአማራ ሶስት የሜትሮፖሊታን ከተሞችን በአዲስ መልክ እየተደራጁ ነው

በአማራ ክልል የሚገኙ ሶስት የሜትሮፖሊታን ከተሞችን በአዲስ አወቃቀር መልሶ ለማደራጀት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር እንደገለጹት ፤በክልሉ የባህርዳር፣ ጎንደርና ደሴ ከተሞች በሜትሮፖሊታንት ደረጃ የተዋቀሩ ናቸው ።

መልሶ ማደራጀቱ መንግስታዊ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

ከተሞቹ ከዚህ በፊት በከተማ አስተደዳርና ክፍለ ከተሞች የነበረውን አወቃቀር የክፍለ ከተሞችን ቁጥር በመቀነስ በስራቸው ቀበሌዎች እንዲኖሩ ተደርጎ ለማዋቀር የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

ከተሞቹን እንደገና ማደራጀት ያስፈለገውም የህዝብ ቁጥር እያደገ በመምጣቱና ህብረተሰቡ በየጊዜው የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ነው።

እንዲሁም በከተማ አስተዳደርና ክፍለ ከተማ ብቻ የተወሰነውን መንግስታዊ አገልግሎት ይበልጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሚታየውን መጉላላትና ምልልስ ለማስቀረትና እርካታ ለመፍጠር ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

''ከመጭው ሐምሌ ወር ጀምሮ አደረጃጀቱ ተግባራዊ ሲደረግ የአገልጋይነት ስሜትን የተላበሱ፣ አቅምና ችሎታ ያላቸውን አመራሮችና ባለሙያዎች ለይቶ በየደረጃው ለመመደብ ትኩረት የሚሰጥ ይሆናል'' ነው ያሉት ።

መንግስት በከተማው ቀበሌዎችን  ለማደራጀት የጀመረው ስራ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከምንጫቸው ለመፍታት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው የሹም አቦ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ መስፍን አስማማው ገልጸዋል፡፡

''የአገልግሎት አሰጣጡ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በሆነ ቁጥር በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎች ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል'' ብለዋል።

በግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትብለጥ ወንድሙ በበኩላቸው '' የቀበሌ አደረጃጀት ህብረተሰቡ የተፋጠነ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል-(ኢዜአ)፡፡