ኦህዴድ የሕዝቡን ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለመመለስ ቁርጠኛ ነው 

 

የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የህዝቡን ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አስታወቁ።

የድርጅቱ 27ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከብሯል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ "ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደቀጣይ ምዕራፍ ያሸጋገረ ድርጅት ነው" ብለዋል።

ድርጅቱ ባደረገው መራርና ውስብስብ ትግል አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የተመለሰ ሲሆን "በተለይ በፖለቲካና በትምህርት ረገድ የተጎናጸፈው ድል ቀላል አይደለም" ብለዋል።

"እንዲያም ሆኖ የኦሮሞ ህዝብ አሁንም ብዙ ጥያቄዎች አሉት፤ ድርጅቱ ጥያቄዎቹን መመለስ መቻል አለበት" ነው ያሉት።

ባለፉት 27 ዓመታት የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው "ከፊታችን የሚጠብቀንን ትግል በቁርጠኝነት ለማለፍ በተሃድሶ ውስጥ አልፈን ለህዝቡ ቃላችንን አድሰናል" ሲሉ ተናግረዋል።

"በመሆኑም አሁን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየተንቀሰቀስን መሆኑን ለሕዝቡ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ" ብለዋል ምክትል ሊቀመንበሩ።

ዶክተር ወርቅነህ ለድርጅቱ አባላት፣ ለኦሮሞ ህዝብና ለእህት ድርጅቶች ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከኦህዴድ ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ኦህዴድ ውስብስብና ተስፋ አስቆራጭ ትግል አልፎ አኩሪ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል" ያሉት ደግሞ የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በከር ሻሌ ናቸው።

እንደ አቶ በከር ገለጻ አሁንም ብዙ ቀሪ ስራዎች በመኖራቸው ትግሉ ቀጣይ ይሆናል።

ድርጅቱ በውስጡ ያሉ ችግሮችን የውስጠ ዴሞክራሲ ባህሉን በማዳበር እየፈታና የህዝቡንም ጥያቄ እየመለሰ እንደሚሄድ ገልጸዋል።

አስተያየት የሰጡ የድርጅቱ አባላት በበኩላቸው እስካሁን ጥሩ የሚባሉ የልማት ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

በተለይም የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን መቅረፍ፣ የአገልጋይነት መንፈስን ማጎልበትና በጊዜ የለኝም መንፈስ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አባላቱ ግንባር ቀደም ሆነው ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል -(ኢዜአ) ።