በግብፅ የኮፕቲክ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ንጹሃን ዜጎች ሕይወታቸውን በማጣታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለግብጽ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ ዛሬ በላኩት የሐዘን መግለጫ በሀገሪቱ ታንታና አሌክሳንድሪያ ከተሞች በንፁሃን ዜጎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ያደረሰውን የሽብር ድርጊት አውግዘዋል።
የሽብር ጥቃቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ የሚገባው ኢ – ሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
መላው ዓለም የጸረ-ሽብር ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ለግብፅ ህዝብና መንግስት እንዲሁም በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሁሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ መፅናናትን ተመኝተዋል።
አሌክስንድሪያ ከተሞች ባሉ ቤተ ክርስቲያናት የሆሳዕናን በዓል እያከበሩ በነበሩ የኮፕቲክ ክርስቲያን አማኞች ላይ በደረሰ ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ከ100 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሽብር ጥቃት አይ ኤስ በመባል የሚታወቀው አሸባሪ ቡድን ኃላፊነቱን መውሰዱን አስታውቋል ።