ከሱዳን በመግባት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ህዳሴው ግድበ የሚያቀኑ ተከርካሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በማቀድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቤህነን ጸረ ሰላም አባላት ጥፋተኛ ተባሉ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ነው ትናንት ተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያሳለፈው።
ተከሳሾቹ በኤርትራ ሃረና አካባቢ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ የሚኖሩት 1ኛ ተከሳሽ አብዱልዋሃብ መሃዲኢሳ እና 2ኛ ተከሳሽ አብዱርሃማን ናስርን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ናቸው።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክሰ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ በኤርትራ ወታደራዊ ሰልጠና በመውሰድ በ2006 ዓ.ም ወደ ህዳሴው ግድብ የሚያቀና ማንኛውም ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅደው 12 ሆኖው ሙሉ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ በሱዳን አድርገው ቤኒሻንጉል ገብተዋል።
ጥቅምት 26 2006 ዓ.ም በሸርቆሌ ወረዳ ሼዲ አሸሸል ቀበሌ በህዘብ ትራንስፖርት ላይ ቦምብ በመወረወር የዘጠኝ ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ እንዲሁም በአራት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማደረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።
እንዲሁም በሚያዚያ 4 2006 ዓ.ም ደግሞ በአካባቢው እጣን ማውጣት ስራ ላይ የነበሩ ሶስት ወጣቶችን የገደሉ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠቀሙበትን አምቡላንስ ማቃጠላቸውን አቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።
በዚህም በአጠቃላይ በፈጸሙት የሽብር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በተከሰሱበት ወንጀልም አቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው በዛሬው እለት ጥፋተኛ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ለቅጣት ውሳኔ ለመስጠትም ለሚያዝያ 4/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።