በትናንትናው ዕለት በተካሄደው 8ኛው ዙር አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የፓርቲዎች የድርድርና አሠራር ደንብ ፀደቀ ።
በፓርቲዎቹ ውይይት ወቅት የአደራዳሪ፣የታዛቢ ፣ ስነ ምግባር፣ የሚዲያ ፣ የውስጣዊ አደረጃጃትና የግብዓት አቅርቦትና የመደራደሪያ ቦታን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሓሳቦች በፓርቲዎቹ ተሠንዝረዋል ።
በተለይ አደራዳሪ ማን ይሁን ፣ የሚዲያ ሽፋንና የመደራደሪያ ቦታው የት ይሁን የሚሉት ነጥቦች ትኩረት ተሠጥቷቸው ጥልቅ ክርክር የተደረጉባቸው ጉዳዮች ናቸው ።
የፓርቲዎቹ አደራዳሪ ከሦስተኛ አካል ውጭ ከራሳቸው ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላትን በመመርጥ ለመደራደር ተስማምተዋል ።
ሆኖም ማን እንዴት ያደራድር በሚለው ሐሳብ ከፓርቲዎቹ መካከል መኢዴፓ ያልተስማማ በመሆኑ ምክንያት ሐሳቡ በልዩነት እንዲመዘገብለት ተደርጓል ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር ከመግባታቸው በፊትና ከድርድሩ ከወጡ በኋላ ለሚዲያ የሚሠጠው መረጃ በሚመለከተው አካል ብቻ መሠጠት እንዳላበት በውይይቱ ተስማምተዋል ።
የፓርቲዎቹ ድርድሩ የት ይሁን በሚለው ነጥብ ላይ ኢዴፓና መኢአድ ለነጻነትና ለገጽታ ግንባታ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ወይም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መሆን አለበት የሚል አቋም አንፀባርቀዋል ።
ቅንጅት ፣ አንድነት ፣ አትፓ፣ ኢራፓ እና ኢህአዴግ ከሉዓላዊነት አንፃር የተለያዩ ሓሳቦችን በማንሳታቸው ድርድሩ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይካሄድ የሚለው ሚዛን በመድፋቱ በምክር ቤት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል ።