በመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል ያለምንም ስጋት እንዲከበር ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ለዋሚኮ እንደገለጹት የዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ከዋዜማው አንስቶ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ለማድረግ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅቶችን በሙሉ አጠናቋል ።
ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ በሚበዛባቸው የገበያ ፣ የመዝናኛና የትራንስፖርት ሥፍራዎች ላይ በቂ ቁጠጥርና ክትትል ለማድረግ እንዲቻል ኮሚሽኑ ዝግጅቶች ሲያካሄድ መቆየቱን ኮማንደር ፋሲካው ተናግረዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመቆጣጣር ከዋዜማው አንስቶ የትራፊክ ፖሊሶች እንደሚሠማሩ የገለጹት ኮማንደር ፋሲካው የትራፊክ ፍሰት መስተጓገል እንዳይፈጠር በአግረኛ ፣ በሞተረኛና በተሽከርካሪ የታገዘ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል ።
ህብረተሰቡ በአቅራቢያው አጠራጣሪ ነገሮችን በሚያይበት ጊዜ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ የነጻ የስልክ መሥመሮች የሆኑትን 991 እና 0111 1101 11 የስልክ መሥመሮችን በመጠቀም ወዲያውኑ ለፖሊስ እንዲያሳውቅ ኮማንደሩ ጥሪ አቅርበዋል ።
በመጨረሻም ኮማንደር ፋሲካ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የሰላም ፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል ።