በአዲስ አበባ ከተማ የማስተር ፕላኑን በጣሰ መልኩ በሰሚት አካባቢ ከ2ሺ 500 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ለግለሰብ መሥጠቱን በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ ።
በአዲስ አበባ የሰሚት አካባቢ ነዋሪዎች ለዋልታ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሠረት ለአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችን ለማከናወን ከተቀመጠው 11ሺ880 ካሬ ሜትር መሬት ውስጥ 2ሺ 500 ካሬ ሜትር በላይ የሚሆነው ለግለሰብ ተሠጥቶ ግንባታ ተጀምሮበታል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ማስተር ፕላን በሚጻረር መልኩ የተጀመረውን ግንባታ ማስቆም ሲገባው በዘንድሮ ዓመት ግንባታው እንዲጠናቀቅ ድጋፍ መሥጠቱ አጠያያቂ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለዋሚኮ ባቀረቡት ቅሬታ ገልጸዋል ።
ለዓመታት የማስተር ፕላኑን መሠረት በማድረግ ለአካባቢው ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማትን ለመገንባት ዲዛይን በማስጠናት ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም እንዲያለሙት አለመፈቀዱንና ህገወጥ ግንባታውን አስተዳደሩ ማፍረስ እንዳልቻለ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።
የነዋሪዎች ቅሬታን ተከትሎ ዋሚኮ ለቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት አስተዳደር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተሠጠው ምላሽ የማስተር ፕላን መጣስ በምንም መልኩ ቢሆን ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ ለመሥጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል አልዩ በበኩላቸው ቦታው የተሠጠው በ1998 የባለአደራ ቦርድ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል ።
እንደ አቶ ጀማል ገለጻ በቅርቡ በድንቡ መሠረት ግንባታው እንዲጠናቀቅ የሚያዝ ድጋፍ መጻፋቸውንና ነገር ግን ግንባታው ማስተር ፕላን እንደሚጥስ ከተረጋገጠ ግን ግንባታው እንደሚፈርስና ካሳም እንደሚሠጥ ተናግረዋል ።