የግል መገናኛ ብዙሃን ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር ያከናወኑት ስራ አነስተኛ መሆኑን የኢትየጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትየጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት በመወጣትና የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት ረገድ የንግድ መገናኛ ብዙሃን የሚገኙበትን ሁኔታ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም ፤ባለስልጣኑ በሀገሪቱ በሚገኙ ሚዲያዎች ላይ ፍተሻ የማድረግ እና ግብረመልስ የመስጠት ሀላፊነቶች አሉበት ብለዋል።
በዚህም መሰረት በሀገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ባለፉት ሁለት ወራት አየር ላይ ያዋሏቸው ዜናዎች እና ፕሮግራሞች ላይ ፍተሻ መደረጉን አስታውቀዋል።
በፍተሻውም በሀገሪቱ የሚገኙ 40 የግል መገናኛ ብዙሃን የተላለፉ 750 ዜናዎች እና 800 ፕሮግራሞች ተፈትሸዋል።
ከዚህም አንጻር በጥሩ መልኩ የታዩት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን እና ሜጋ ፕሮጀክቶች ከህብረተሰቡ ጋር እንዲተዋወቁ ከማድረግ አንጻር ጥሩ የሚባል ስራ ሰርተዋል ተብሏል።
በወቅታዊ እና አካባቢያዊ ጉዳይ ላይም መልካም ስራ መስራታቸውም ነው የተገለፀው።
ሆኖም ግን ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር እና እቅድ ቀርፆ ከመስራት አንጻር ውስንነቶች ታይተዋል።
እንዲሁም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ሀላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ዳር ላይ ሆነው ይመለከታሉ የሚለውም ተነስቷል።
ስፖርት ላይ ማመዘን እንዲሁም ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር ውስንነቶች እንደሚታዩባቸው ተገልጿል።
እነዚህን ክፍተቶች ለመፍታትም መገናኛ ብዙሃኑ ለህግ እና ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን የሙያ እና የቴክኒክ አቅማቸውን መገንባት ያስፈልጋል ነው ያለው ባለስልጣኑ።
ባለስልጣኑ ተከታታይነት ያለው የአመለካከት እና የክህሎት ስልጠና መስጠት እንዳለበት በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
የመገናኛ ብዙሃኑ የብሮድካስት ፍቃድ ሲወስዱ ያቀረቡትን እቅድ በመተግበር ረገድም ውስንነቶች ይስተዋላሉ ተብሏል።
እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የመረጃ ነፃነት አዋጅ ውስጥ የተዘረጉት የተጠያቂነት አሰራሮች ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚገባም ተገልጿል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።