በሳዑዲ ለኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የመውጫ ቪዛ የሚሰጡ ጽህፈት ቤቶች ተከፈቱ 

 

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶች መከፈታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳዑዲ መንግስት ካለፈው መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሁሉም አገራት ዜጎች በ90 ቀናት ከአገሪቷ እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳስታወቁት፤ መንግስት የዜጎቹ ደህንነት ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ  ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ነው።

በቅርቡም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ገብረሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በማቅናት የአራት ቀናት ቆይታ አድርጎ ተመልሷል።

ቡድኑ በቆይታው ተመላሽ ኢትዮጵያውያኑ የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት መውጣት በሚችሉበት ሁኔታ ከሳዑዲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል።

በዚህም ኢትዮጵያውያኑ ሳይቸገሩ የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳዑዲ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ እንደተቻለ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በሪያድና ጂዳ የሚሲዮን ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ብቻ ይሰጥ የነበረው የቪዛና የጉዞ ሰነድ በየአካባቢው በተከፈቱ ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶች የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ እንዲያገኙ ይደረጋል።

ቡድኑ በአገሪቷ ከሚገኙ የኮሚኒቲና የልማት ማህበራት እንዲሁም ከዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር መምከሩንም ገልጸዋል ቃል አቀባዩ።

ተመላሾቹ እንግልት ሳይደርስባቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በእስካሁን ሂደት በጽሕፈት ቤቶቹ አራት ሺህ ስደተኞች የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ሲሆን ከመካከላቸው 200 ያህሉ ወደ አገራቸው ገብተዋል።

መግባት ከሚገባቸው ስደተኞች አኳያ ሲታይ ቁጥሩ በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል አቶ መለስ።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን አዋጁን የተመለከቱ መረጃዎችን በመስጠት ዜጎቻችን ተግባራዊ ባያደርጉ ሊገጥማቸው የሚችለውን ጉዳት በመዘገብ የችግሩን አሳሳቢነት ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል።

የሳዑዲ መንግስት ህገ-ወጥ የሚላቸው ድንበር አቋርጠው የገቡ፣ ቋሚ ቦታ የሌላቸው፣ የስራና የመኖሪያ ፈቃዳቸው ጊዜ የተጠናቀቀ እንዲሁም የስራ ፈቃድ ኖሯቸው የመኖሪያ መታወቂያ የሌላቸው፣ ለሃጂና ኡምራ ሂደው የቀሩና የሃጂ ጉዞ ያለ ፈቃድ ያደረጉ ናቸው።

በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሲኖሩ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተገልጿል።

የሳዑዲ መንግስት አዋጁን ያወጣው የአገሪቱ የገቢ ምንጭ የሆነው የነዳጅ ዘይት ዋጋ በየጊዜው በመዋዠቁ፣ በአካባቢው እያንዣበበ ከመጣው የአሸባሪነት ስጋት ጋር ተያይዞም የህገ-ወጥ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሔዱ እንደሆነ ተነግሯል (ኢዜአ) ።