በትግራይ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሱ 114 ግለሰቦች ከአንድ እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የክልሉ የጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን አስታወቀ።
ግለሰቦቹ በፈጸሙት የሙስና ወንጀል ተመዝብሮ የነበረው ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ ተደርጓል፡፡
የእስር ቅጣቱ በግለሰቦቹ ላይ የተላለፈው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በመንግስትና በግል ስራ ላይ ተሰማርተው ሰጪና ተቀባይ በመሆን የከተማ መሬት ያለ አግባብ ሲዘርፉና ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በማስረጃ ስለተረጋግጠባቸው ነው፡፡
የክልሉ የጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃነ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በእስራት ከተቀጡት ግለሰቦች መካከል በተለይ በቅየሳና በግንባታ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችና የመንግስት የምህንድስና ባለሙያዎች ያልተገባ ውልና ክፍያ እንዲፈፀም ያደረጉም ይገኙበታል፡፡
ተመላሽ ከተደረገው ገንዘብ በተጨማሪም በመቀሌ ከተማ በመንግስት ሃብትና መሬት አለአግባብ ተገንብተው የነበሩ ሶስት ዘመናዊ ቪላ ቤቶችም ተሽጠው ለመንግስት ገቢ እንዲሆን በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
" ሙስናን ማስወገድ የሚቻለው ድርጊቱን የሚጠላ ዜጋ ማፍራት ሲቻል ነው " ያሉት ኮሚሽነሩ ፣ ቅጣት የመጨረሻ መፍትሄ ባይሆንም በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሯሯጡ ግለሰቦች ከተገኙ ግን እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ሙስናን የሚጠየፍ ዜጋ ለማፍራት በ52 የክልሉ ወረዳዎች ውስጥ አምስት ሺህ 500 ለሚሆኑ የህዝባዊ ማህበራት፣የመንግስትና የግል ተቋማት ተወካዮችና በየትምህርት ቤቱ ለተቋቋሙ የጸረ ሙስና ክበባት አመራሮች የግንዛቤ ትምህርት መስጠቱን አመልክተዋል።
የልማትና የእድገት ፀር የሆነውን ሙስና ይበልጥ ለመታገል ኮሚሽኑ የዞንና የወረዳ መዋቅር እንዲኖረው ለማድረግ ጥናት እያካሄደ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም አንድ ሺህ 189 የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ያላቸውን ሃብትና ንብረት ወደ ኮሚሽኑ ቀርበው አስመዝግበዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታትም ከ10 ሺህ በላይ አመራሮችና ባለሙያዎች ሃብታቸውን እንዳስመዘገቡ ተመልክቷል።
በመቀሌ የሰሜን ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ ወጣት አንገሶም መለስ በሰጠው አስተያየት" የክልሉ የጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ሙስናን ለመታገል በሚያስችለው የሰው ሃይልና የገንዘብ አቅም መጠናከር አለበት" ብለዋል።
በክልሉ የሚታየውን የሙስና ወንጀል ለመታገል የፀረ ሙስና ክበቦችና ጥምረቶችን በማጠናከር መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ ዓይደርና በሰሜን ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ ወጣት ብርሃን ሃፍታይና ወጣት ስምረት ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳመለከቱት የሙስናን አስከፊነት በመገንዘብ ለመታገል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡