የታንዛኒያ አየር መንገድ 28 አብራሪዎችን ለተጨማሪ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መላኩን አስታወቀ ።
የታንዛኒያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ላዲስለስ ማቲንዲ እንደገለጹት ለአብራሪዎች ሥልጠና ኢትዮጵያን ተመራጭ ያደረግነው ወደ እንግሊዝ እና ካናዳ ልከን ከምናወጣው ወጪ በሰዓት አምስት መቶ የአሜሪካን ዶላር ስለምናተርፍ ነው ብሏል፡፡
የኢትዮያ አየር መንገድ የራሱ የሥልጠና እና የጥገና ማዕከል ያለውና ለሌሎችም የአፍሪካ አገራት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ለተመራጭነቱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
አብራሪዎቹ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የታወቀ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸውን ሠልጣኞች ሲልክ የመጀመሪያው ሲሆን ከዚህ ቀደም በየዓመቱ እንደሚያሰለጥን እንደነበር ታውቋል፡፡
በተያዘው ዓመት እንኳ 18 ያህል የበረራ ሰልጣኞችን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የታንዛኒያው ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታንዛኒያ ዳሬሰላም፣ ዛንዚባር እና ኪሊማንጃሮ ሦስት መዳረሻዎች እንዳሉት ዘገባው አስታውሷል፡፡