አዲስ አበባ ከአደጋ ነፃ የሆነ የፋሲካ በዓል ማሳለፏን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ ከተማ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እና ከአደጋ ነፃ የሆነ የፋሲካ በዓል ማሳለፏን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለጹት፤ ከበዓሉ ዋዜማ አነንስቶ እስከ መጠናቀቂያው ምንም አይነት የፀጥታ ችግር አልተከሰተም፡፡

በበዓሉ እለትም የተመዘገበ የትራፊክ አደጋ እንደሌለ ነው አክለው የጠቆሙት ፡፡

ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር አካባቢውን በንቃት ሲከታተል እንደነበረ ያስታወቁት ኮማንደሩ ነዋሪውን ስለ ትብብሩ በአዲስ አበባ ኮሚሽን ስም አመስግነዋል፡፡

በተመሳሳይ ህብረተሰቡ በየመገናኛ ብዙኃኑ የተላለፈውን መልዕክት ተግባራዊ በማድረግ ከአደጋ ነፃ የሆነ በዓል ለማሳለፍ ተችሏል ሲሉ አቶ ንጋቱ ማሞ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ለጣቢያችን ግልጸዋል፡፡

በመደበኛው ቀን ያጋጥም የነበረው አደጋ እንኳ በዚህ በዓል አልተመዘገበም ያሉት ባለሙያው፤ ህዝቡ ከበዓሉ ድባብ አሁንም ያልተላቀቀ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡