የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች አካባቢዎች ተነስቶ በነበረው ሁከት መንስኤና የተወሰደው እርምጃ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች አቀረበ ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ባቀረቡት ሪፖርት ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖች እና 91 ከተሞች፣ በአማራ ክልል 5 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በሚገኙ 6 ከተሞች ምርመራ ማድረጉን አስታውቀዋል ።
በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ሁከት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ህገመንግስቱ በሚደነግገው መሰረት ተግባራዊ አለመደረጉ እና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዋነኛ መነሻ መሆናቸውን ገልጿል ።
በአማራ ክልል ለተከሰተው አመፅ ደግሞ፣ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም የሚሉ ጥያቄዎች፣ የትግራይ የበላይነት አለ የሚሉ ቅሬታዎች፣ የዳሽን ተራራ በመማሪያ መፅሐፍ ውስጥ በትግራይ ክልል ስር እንዲካተት መደረጉ፣ የጠገዴ ወሰን ድንበር ምላሽ ያግኝ እና የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚሉት ምክንያቶች መሆናቸው አመልክቷል ፡፡
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ለተከሰተው ብጥብጥ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንስኤ መሆናቸው ጠቁሟል ፡፡
በዚህም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን) እና ማህበራዊ ድረገጹ ሃምሌ 30 እና ነሃሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ሰፊ የአመፅ ጥሪ ማድረጋቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ይህን ተከትሎም የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ ሐይቅ በሚከበርበት ወቅትም የአመፅ ጥሪ በተመሳሳይ ኃይሎች ተደርጓል ነው ያለው ፡፡
ኢሬቻ በዓል ላይ ለተፈጠረው አመጽ የጸጥታ ኃይሉ ከአስለቃሽ ጋዝ ውጭ የተጠቀመው የኃይል እርምጃ እንደሌለ የተጠቀሰ ሲሆን፤ የተወሰደው እርምጃም ተመጣጣኝ ነው ብሏል፡፡
በምዕራብ አርሲ፣ ባሌ እና ጉጂ በትጥቅ የታገዘ ሁከት መፈጸሙ ጠቁሞ ፤ የጸጥታ ኃይሉ የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለማዳን የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና አስፈላጊ እንደነበር ነው ያረጋገጠው ፡፡
በባሌ ሮቤ እና በምስራቅ ሀረርጌ 28 ሰዎች የሞቱበት እንዲሁም በዲዴሳ ከተማ የተካሄደው እርምጃ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን የፀጥታ ኃይሉ የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑ አመልክቷል ፡፡
በኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ)፣ በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የተመሩት ህገወጥ ሰልፎች፥ የብሔር ጥቃትን ማድረሳቸው፣ የሃይማኖት እኩልነትን መናዳቸው፣ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት የጣሱ እና የአካል ጉዳትን ያደረሱ መሆናቸው ነው ያብራራው ፡፡
አመጹ 462 ሰላማዊ ሰዎችና 33 የፀጥታ ኃይሎች በድምሩ 495 ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው፡፡
የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ጊዜ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል በቂ መረጃ እያላቸው ጥንቃቄ እና በቂ ጥበቃ አለማድረጋቸው ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን ገልጿል፡፡
የጸጥታ ኃይሉ በበዓሉ ወቅት ያሳየው ትዕግስት የሚስመሰግን ቢሆንም በማግስቱ በቢሾፍቱ የነበረውን ብጥብጥ ባለመቆጣጠሩ ሊጠየቅ ይገባል ብሏል ።
በአዳሚ ቱሉ 14 ሰዎች ለሞቱበት፣ በአወዳይ እና ዲዴሳ ለ38 ሰዎች ሞት እና ለ62 ሰዎች መጎዳት ምክንያት የሆኑ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስቱ እና የኦሮሚያ ክልል በጋራ የዘር ጥላቻ፣ የሃይማኖት አክራሪነትንና የብሔር ጥቃትን ለመከላከል ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያመለከተው ፡፡
በአማራ ክልል ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ በተሞከረበት ጊዜ የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ለማዳፈን ነው በሚል ኢሳትን በመሳሰሉ የሽብር መጠቀሚያ ሚዲያዎች መልዕክቶች ተላልፈዋል ብሏል፡፡
በክልሉ የተደረጉ ሰልፎችም ህጋዊ ፍቃድን ያላገኙ እንደነበሩም ነው የገለጸው፡፡
የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የማቃጠል እና የብሔር ጥቃት መፈጸሙንም አረጋግጧል ፡፡
ከሚሽኑ በአመጹ 110 ሰላማዊ ሰዎች እና 30 የፀጥታ ኃይሎች በአጠቃላይ 140 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
እንደዚሁም በ236 ሰላማዊ ሰዎች እና በ100 የፀጥታ ሀይል አካላት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል ።
በአጠቃላይ በአማራ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ሁከት 669 ሰዎች መሞታቸውን ነው የገለጸው ።
እንዲሁም 111 ሚሊየን 417 ሺህ ብር የንብረት ውድመት መድረሱንም ገልጿል፡፡
በሁከት እና ብጥብጡ ወቅት የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ የመረመረው ኮሚሽኑ፤ የጸጥታ ኃይሉ በአብዛኛው ስፍራዎች ተመጣጣኝ እርምጃ ቢወስድም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን አላስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰዱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል ።
ከሚሽኑ ሐምሌ 18 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ማራኪ የተወሰደው እርምጃ ህጋዊ እና ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም በባህርዳር ማረሚያ ቤት፣ በጅጋና በሊቦ ከምከም እና ሌሎችም ቦታዎች የተወሰዱት እርምጃዎች ተመጣጣኝ መሆናቸውን ነው ያረጋገጠው ፡፡
በደምቢያ መንገድ በዘጉና በደባርቅ፣ በወገራ፣ በደብረታቦር መኪና ላይ ድንጋይ የወረወሩ ግለሰቦች፣ በስማዳ፣ በእብናት፣ በወረታ ሁለት ሰዎች የሞቱበት፣ እና በዳንግላ የጸጥታ ሃይሉ አላስፈላጊ የሃይል እርምጃ ወስዷል ብሏል፡፡
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በተደረጉ ህገወጥ ሰልፎች፣ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥም የ34 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሲሆን 139 ሰዎችም ተጎድተዋል፡፡
ኮሚሽኑም በሌሎች ብሔሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ያደረሱ አካላት፣ በአመጹ ተሳታፊ የነበሩ የጌዲዮ ዞን የአስተዳደር፣ የፖሊስ አካላት፣ እና የጌዲዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መጠየቅ አለባቸው ብሏል፡፡
በሌሎች ብሔሮች ላይ የተካሄደውን ጥቃት የተቃወሙ የጌዲዮ ተወላጆች እንዲቋቋሙ የሚደረግበትን መንገድ ዞኑ እና ክልሉ በጋራ እንዲሰሩ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በዞኑ የአመጹ ዋነኛ መነሻ የሆነው የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመከበርም እንዳይደተገም ነው ያስጠነቀቀው ፡፡
ኮሚሽኑ የመልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር፣ ንብረት የወድመባቸውን ማቋቋም፣ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል፣ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ የወሰዱ የጸጥታ አካላትን እንዲጠየቁ ማድረግና የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ማስከበር መፍትሄዎች አቅርቧል፡፡