ካናዳ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

 

 ካናዳ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በካናዳ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ተጠሪ ሚስተር ኦማር አልግሃብራ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በካናዳ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ተጠሪ ሚስተር ኦማር አልግሃብራ የተመራ ልኡካን ቡድንን በቢሯቸው ተቀብለው ዛሬ አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ፍሊፕ ቤከር እንደገለጹት፤ ልኡካን ቡድኑ አገሮች ካሁን በፊት የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በካናዳ የልማት መርሃ ግብር ድጋፍ ከሚደረግላቸው አገሮች አንዷ መሆኑዋን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ የልዑካን ቡድኑ መሪ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን አብራርተዋል።

ሁለቱ አገሮች ከልማት ትብብር በተጨማሪ የፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የተናገሩት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ተበጀ በረሄ ናቸው።

በተለይም ሁለቱ አገሮች የፌዴራሊዝም ስርዓት የሚመሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞበዘርፉ ልምድ የሚለዋወጡበትን ሁኔታዎች ለማጠናከር መክረዋልብለዋል።

በኢትዮጵያ በኃይልና ማዕድን ዘርፍ የሚታዩ የአቅም ውስንነትን ለመፍታት ካናዳ የምታደርገውን ትብብር በምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን አመልክተው፤ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያላቸውን ግንኙነትም በሚያጠናክሩበት ስልት ላይም መምከራቸውን ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገልፀዋል።

ካናዳ ለኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በማዕድንና ሃይል ዘርፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚውል ድጋፍ ከምታደርግባቸው ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ካናዳ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚውል ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደምታደርግ ታውቋል-(ኢዜአ) ።