Skip to content
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግስታት መካከል አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ስመምነት ተፈራርመዋል ፡፡
ይህ ዛሬ በፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ የተከናወነው ስምምነት በሁለቱም ክልል መንግስታት በሚገኙ በመስራቅ በምዕራብ ሀረርጌ ፣ባሌ ዞኖች እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በፈፋን ፣ሲቲ ፣አፍዴር እና ነጎብ ዞኖች ስር በሚገኙ አዋሳኝ ወረዳዎች አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ውሳኔ መሆኑ ነው የተመለከተው ፡፡
የስምምነት ሰነዱ ዓላማም በሁለቱም ክልሎች ስር የሚገኙ ሰባት አዋሳኝ ዞኖች መካከል አስተዳር ወሰን ጋር ተያይዞ ይከሰቱ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት አጎራባች ማህበረሰቦችን በማልማትና በመልካም አስተዳደር በማስተሳሰር ተጠቃሚ ለማድረግ እንደዚሁም የአከባቢውና የሀገሪቱን አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መሆኑ ነው የተገለጸው ፡፡
ከአጠቃላይ ስምምነቱም ውስጥ በ1997 ዓም ህዝበ ውሳኔን ተከትሎ የተደረሰውን አስተዳደራዊ ወሰን ስምምነት ሁለቱም ክልሎች ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸው ይጠቀሳል ፡፡
ስምምነቱ የኢፌዲሪ ህግ መንግስትን እና እርሱን መነሻ አድረገው የወጡ ህጎችን መሰረት ያደረገና ዲሞክራሲያዊ አንደነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማመተናል የሚልም ይገኝበታል ፡፡
ይህም ሁለቱም ክልሎች የስምምነቱን ሰነድ በተፈራረሙ ከ3 ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኑን ለህዝብ ይፋ በማድረግ እንደሚያጠናቅቁ ነው ያስታወቁት ፡፡
በመድረኩ የተገኙት የፌደራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ወሰኑ ባለመካለሉ እስካሁን ድረስ ብዙ ህይወት መቅጠፉን አስታውሰው አሁን ግን ስምምነቱ ችግሩን ከመሰረቱ የሚፈታ ከመሆኑም ባሻገር ዘላቂ ሰላምና አንድነትን የሚፈጥር መሆኑን አስገንዘበዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ሱማሌ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው ይህ ምዕራፍ ለኦሮሚያም ሆነ ለሶማሌ ህዝብ ሰላም ፣ልማትና ፍላጎትና የህዝቦቸ አንድነት ያነጣጠረ ውሳኔ ስለሆነ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ከዛሬ ዓመት በፊት ችግሩን መፍታት ይቻል የነበረ ቢሆንም አመራሮች በየጊዜው በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት አስካሁን መቆየቱን ገልጸው አሁን ግን በቁርጠኝነት ለመፍታት መነሳታቸውን አረጋግጠዋል ፡፡
የሁለቱም ክልሎች ስምምነት መፈጸም ለጸረ ህዝቦች መርዶ ለህዝቦቹ ደግሞ የምሰራች መሆኑን ነው የተመለከተው ፡፡