የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ወደ ክልሉ ሰርገው የገቡ ፀረ ሠላም ኃይሎችን አድኖ በመያዝና አሳልፎ በመስጠት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጠ።
በአሶሳ ከተማ ከትናንት በስትያ በተካሄደው የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የክልሉ የፀጥታ አባላት ከገንዘብ ስጦታ እስከ ማዕረግ እድገት የደረሰ እውቅና ተሰጥቷል፡፡
እንደዚሁም 82 የክልልና የፌደራል ተቋማት እውቅና አግኝተዋል ።
በስ-ነስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለፁት፤ " ሠላምና የህዝብ ደህንነት በተረጋገጠበት ባለፉት 25 ዓመታት ፈጣን እድገት ማስመዝገባችን ሲታይ የሰላምን ውድ ዋጋ ከኛ በላይ ሊረዳና ሊያስረዳ የሚችል አካል የለም" ብለዋል፡፡
ይሁንና የሀገሪቱ ልማትና እድገት እረፍት የሚነሳቸው የውስጥና የውጭ ፀረ ሠላም ኃይሎች ነውጥና ብጥብጥ በመፍጠር የህዳሴውን ጉዞ ለማሰናከል ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም ሲሉ ጠቅሰዋል ፡፡
አመቺ ጊዜና ወቅት እየጠበቁ የሽብር ተግባራቸውን ለመፈፀም የሚያደርጉት ሙከራ በጸጥታ ኃይሎች ጥምረትና በህዝብ ተሳትፎ እየከሸፈ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የክልሉን ሠላም ለማናጋትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ በተያዘው ዓመት የገቡትን እራሱን የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት መደምሰስ መቻሉን አስታውሰዋል።
የፀረ ሠላም ኃይሎችን ለመደምሰስ በተደረገው ትግል ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የትግል አጋርነታቸውን ላረጋገጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ላቅ ያለ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡
"ከክልሉ ጋር በስፋት የሚዋሰነው የሱዳን ብሉ ናይል ግዛት መከላከያ ሠራዊት አባላትና ህዝብ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን አድኖ በመያዝና አሳልፎ በመስጠት ወንድማዊ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል " ነው ያሉት ፡፡
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የ12ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለመደምሰስ የተደረገው ትግል የአንድ አካል ብቻ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡
" በየደረጃው ያለ አመራር ልማት ሲያመጣና መልካም አስተዳደር ሲያሰፍን ህዝቡ ያለው አመኔታ ስለሚያድግ እንኳን ሽፍታ ንፋስ አይገባም " በማለት የመስተዳድር አካላት ከህዝቡ ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸውም ነው ያመለከቱት ፡፡
የክልሉ የፀጥታ አካላት ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመቀናጀት ፀረ-ሠላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን የገለጹት፤ ደግሞ የክልሉ የፀረ ሽምቅ፣ ልዩ ጥበቃና አድማ ብተና ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ፈረደ ቦጂ ናቸው፡፡
በቅርቡ በተደረገው ግዳጅ በየአካባቢው የሚኖረው ህዝብ መረጃ በመስጠትና ፀረ ሠላም ኃይሎች የሚገኙበትን በመጠቆም ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል- (ኢዜአ)፡፡