ምክር ቤቱ በሁከቱ ወቅት ያልተመጣነ እርምጃ የወሰዱ የጸጥታ ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ ወሰነ

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአማራ ፣በኦሮሚያና በደቡብ ክልል አንዳንድ አከባቢዎቸ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላትና አላስፈላጊ  እርምጃ በወሰዱ የጸጥታ ኃይሎችና የተቀዋሚ ፓርቲዎች አባላት ለህግ እንዲቀርቡ ወሰነ ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ዛሬ ያቀረበውን ሪፖርት አጽድቋል ።

ለሁከት እና ብጥብጡ የመልካም አሰተዳደር ችግር ዋነኛ መንስኤ ነው የተባለ ሲሆን፤ በዚህ ተግባር ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚጠረጠሩ በየደረጃው ያሉ የመንግሰት አመራሮች፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ተግባራቸው ተጣርቶ ለህግ እንደሚቀርቡ ነው ምክርቤቱ የወሰነው ፡፡

ከዚህ ባለፈም በጌዲኦ ዞን ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት እና የጌዲኦ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲጠየቁም ወስኗል።

በአማራ ክልል ለተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ በህጋዊነት የተመዘገቡትን የአሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፊኮ)  እና ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ አባላት ለተፈጠረው ቀውሰ የአባባሽ ሚና በመጫወታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ባቀረበው መሰረት ምክርቤቱ እንዲጠየቁ ነው የወሰነባቸው ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ ኮሚሽን በሶስቱም ክልሎች 669 ሰዎችና የጸጥታ ኃይሎች መሞታቸውም በሪፖርታቸው አቅርቧል ፡፡

በብሄር ተኮር ጥቃት ከአካባቢያቸዉ የተፈናቀሉ ዜጎችም በአፋጣኝ እንዲቃቋሙ ነው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያሳሰሰበው፡፡