በአገሪቱ ለሚድያ ትክክለኛ መረጃ መስጠትን ባህል ማድረግ ይገባል -ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

በአገሪቷ የሚከሰቱ ችግሮች የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ "ለሚዲያ ክፍት መሆንና ትክክለኛ መረጃ መስጠትን ባህል ማድረግ አለብን" ሲሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስገነዘቡ ።

ጽሕፈትቤቱ በቀውስ ወቅት ኮሚዩኒኬሽን  ስራዎች ዙሪያ ከክልሎች የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና ከሚዲያ ተቋማት ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በዚሁ መድረክ  ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና በአዲስ አበባ ቆሼ በደረሰው አደጋ የነበረው ልምድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ "በእነዚህ ባሳለፍናቸው የቀውስ ጊዜዎች የሰራናቸው የኮሚዩኒኬሽን  ስህተቶች ጥሩ ልምድ ሊሆኑን ይገባል" ብለዋል።

ቀውስ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ቅፅበታዊ ነገር በመሆኑ ጠንካራ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን  ስራ ካልተሰራ ወደከፋ ሁኔታ ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለሰው ህይወት ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም ዜጋ የደረሰውን ቀውስ፣ ያስከተለውን ጉዳትና እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በፍጥነት ይፋ በማድረግ የሩቁም ሆነ የቅርቡ ትክክለኛ መረጃ አግኝቶ እንዲረጋጋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

ሆኖም ግን በቀውስ ወቅት መንግስትና መገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆኑ ዜጎችም የሚያገኙትና የሚሰጡት መረጃ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ዶክተር ነገሪ አሳስበዋል።

በውይይቱ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተከሰተው ችግር በነበረው የኮሚዩኒኬሽን  ስራ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ለመገናኛ ብዙሃን ቅርብ ያለመሆንና ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ያለመስጠት ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ተገልጿል ።

አንዳንድ የሚዲያ ተቋማትም ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከመስራት ይልቅ ነገሮችን ሲያባብሱ እንደነበረ ሁሉ ፤በተቃራኒው ህዝብ የጠቀሙ መስሏቸው መረጃዎችን የሚሸሽጉ መገናኛ ብዙሃንና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ነበሩም ይፋ ሆኗል  ።

ይህም የተፈጠረውን አለመረጋጋት፣ የህዝብ ቅሬታና ጥያቄ ሌሎች ለሌላ ዓላማ እንዲጠቀሙበት በር ከፍቷል፤ ቀውሱ እንዲባባስም ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው ።

በቅርቡ በመዲናዋ ቆሼ አካባቢ የተከሰተው አደጋ የተመራበት የተቀናጀ የመረጃ አሰጣጥ እንዲሁም በፍጥነትና በግልጽነት ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን እንዲደርስ መደረጉ ጥሩ ልምድ እንደሆነ ተጠቅሰዋል (ኢዜአ) ።