በሳዑዲ አረቢያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 346 የሚሆኑ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በቅርቡ ሳዑድ አረቢያ መንግሥት ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች በሦስት ወር ውስጥ እንዲወጡ ባስተላላፈው መመሪያ መሠረት ነው 346 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው ።
ከስደት ተመላሾቹ 222 የሚሆኑት ቅዳሜ 124ቱ ደግሞ እሁድ ጠዋት ወደ አገራቸው ሲገቡ የመንግሥት ከፍተኛ አመራር አባላት ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባባል አድርገውላቸዋል ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የክትትልና ድጋፍ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አብዱልባሲጥ ከድር እንደገለጹት ከስደት ከተመለሱት ኢትዮጵያውያን መካከል 44 የሚሆኑት ወደ ትውልድ አካባቢዎች ለመሄድ አቅም የሌላቸው በመሆኑ ዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት ተቀብሏቸዋል ።
የዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት ከተቀበላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ሰድስቱ የጤና እክል ያጋጠማቸው በመሆኑ ለስደተኞቹ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አቶ አብዱልባስጥ አስረድተዋል ።
ከሳዑዲ አረቢያ ከተመለሱት ስደተኞች መካከል 292 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች በሳዑዲአረቢያ እስር ቤቶች ቆይታ የነበራቸው ሲሆን 52 የሚሆኑት በራሳቸው ፈቃድ ለመመለስ መብቃራቸውን አቶ አብዱልባስጥ አመልክተዋል ።
ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉና የትራንስፖርት ገንዘብ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ተመዝግበው ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉም ተጠቁሟል ።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትም ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሽ ስደተኞችን ለማስተናገግ በአንድ ጊዜ 200 ሰዎችን መያዝ የሚችል መጠለያ ጣቢያ አቋቁሟል
የተመላሽ ስደተኞቹን ጉዳይ በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ብሔራዊ ግብረ ሃይል የተቋቋመ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሂደቱን እየተከታተለ እንደሚገኝም መገለጹ ይታወቃል።
ከሳዑዲ ተመላሽ ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የይለፍ ሰነድ አግኝተው መጉላላት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችም እየተመቻቹ ናቸው።(ኢዜአ)