ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የመላው አፍሪካን የቅኝ ግዛት ታሪክ የማስተማርና የምርምር ስራን የሚዳስስ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ ፡፡
" የአድዋ ዩኒቨርስቲ ፎር ፓን አፍሪካ ስተዲስ" የኢትዮጵያን ገድል ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካን የቅኝ ግዛት ታሪክ የማስተማርና የምርምር ስራን ይዳስሰዋል ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስት ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የአድዋ ዩኒቨርሲቲ ፎር ፓን አፍሪካን ስተዲስ በሚገነባበት ስፍራ አድዋ ላይ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት የአድዋ ጦርነት ከብረት የጠነከረ ኢትዮጵያዊ አንድነትና የማንነት ጽናት የታየበት ትልቅ ክስተት ነበር፡፡
ኢትዮጵዊያን ከየአቅጣጫው ዘር ፣ ቀለም ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልዩነት ሳይገድባቸው ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ወደ ስፍራው ተንቀሳቀሰዋል፡፡
ይህን ዘመን ተሻጋሪ የአያት ቅድመ አያቶች ታሪክ በአግባቡ በማደራጀት ቀጣዩ ትውልድ የሚረከብበት ሀገር ፣ የገናና ስልጣኔና የአኩሪ ታሪክ ባለቤት መሆኗን እንዲረዳ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡፡
" በአንጻሩም ከገዥዎች የተሳሳተ ፍላጎት የወረስነውንና በመራራ ትግላችን ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ያደረግነውን የተዛባ ግንኙነት አላአግባብ ለማጉላት የሚጥሩ ሃይሎች ያልተገባ እድል ልንሰጣቸው አይገባም" ብለዋል
የአድዋ ታሪክ ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በመላ ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት ስለአድዋ ሰፊ ምርምሮችና የጥናት ውጤቶች ይፋ ሲያደርጉ" የታሪኩ ባለቤት የሆንን እኛ ዓመታዊ ድሉን ከመዘከር ባለፈ ይሄ ነው የሚል ስርተናል ማለት አንደፍርም" ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚነስትሩ እንዳመለከቱት ይህንን ከመሰረቱ ለመቀየር መንቀሳቀስ ይገባል፡፡
ከዚህ አኳያ በዜጎች ግንባር ቀደም አነሳሽነት፣ በአፍሪካዊያን ተሳትፎና በጥቁር ህዝቦች ትጋት ዛሬ በይፋ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
" የአደዋ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ገድል ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ የቅኝ ግዛት ታሪክ በዚህ የማስተማርና የምርምር ስራ ይዳስሰዋል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማያያዝም የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ መሆኑን በመገንዘብ ከተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጡ አባላት ራሳቸውን አንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ የዩኒቨርሲቲውን ሀሳብ በመጠንሰስና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለዪኒቨርሲቲው ግንባታ እውን መሆንም የኢፌዴሪ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ላይ የተሳተፉ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በበኩላቸው የአፍሪካዊያንና የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ኩራት በሆነው አድዋ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ መገንባቱ እውነታውን የሚያሳይ የታሪክና የዕውቀት መገብያ ማዕከል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ጋር በመሆን ነው (ኢዜአ)፡፡