ሶማሊያውያን በባህር ላይ ወንበዴዎች ዝርፊያ ምክንያት ለከፋ ረሃብ እየተጋለጡ ነው -ተመድ

ሶማሊያውያን  በባህር ወንበዴዎች ዝርፊያ ምክንያት ለከፋ  ረሃብ እየተጋለጡ መሆኑን  የተባባሩት  መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ ።

ሶማሊያ በኤልኒኖ ምክንያት ለከፋ ድርቅ ከተዳረጉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተርታ ቀዳሚዋ እንደሆነች የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡

አገሪቱ በአንድ በኩል በአሸባሪዎች ስትናጥ የከረመች ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ተፈጥሯዊ ክስተት ምክንያት መከራዎች  መብዛታቸው ተገልጿል ፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት እና አሜሪካ ለሞቃዲሹ ድርቅና ርሃብ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ቢሆን ሶማሊያውያንን ለመታደግ  ጥረት እያደረገ ይገኛል ።

ነገር ግን ለሶማሊያውያን የተከሰተባቸውን ቀውስ የሚያባብሰው በባህር ላይ  በወንበዴዎች የሚፈጸመው  ዝርፊያ  ተጨማሪ ምክንያት ራስ ምታት መሆኑ ቀጥሏል፡፡

በሶማሊያ የባህር ላይ ውንብድና የአገሪቱን እጣ ፈንታ አሁንም ለከፋ ደረጃ እየዳረገ እንደሆነ የመገናኛ ብዙሃኑ ያትታሉ፡፡

አንዳንዶች እንደሚሉት የባህር ላይ ወንበዴዎች ለመበራከታቸው በሀገሪቱ የተከሰተው ቀውስ መነሻ ነው ይላሉ፡፡ የተደራጁ ወጣቶች አማራጭ ቢያጡ የተሰማሩበት ነው ወጣቶቹ ለቤተሰቦቻቸው እና ለልጆቻቸው ብለው ይዘርፋሉ ሲሉ ይፅፋሉ፡፡

ለዚህ ሀሳባቸው ደግሞ ዘራፊዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርዳታ ቁሳቁሶች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን እንደምክንያትነት ያነሳሉ፡፡

በሌላኛው ወገን የሚነሳው ደግሞ ይህ የአሸባሪዎች ኢላማ ነው የሚል ነው፡፡ አሸባሪዎቹ ሶማሊያንና ሶማሊያውያንን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አገራቸውን እንዳልነበረች ሲያደርጉ ለእነርሱ የሚመጣውን እርዳታ በመቀማትም መከራቸውን ያበዙታል ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡

ቢቢሲ እንዳስነበበው ከእነዚህ ዘራፊዎች መካከል አንዳችም እንኳ የሶማሊያ የዘር ግንድ የሌለውን አላገኘንም፤ ስለዚህ የራሳቸው ልጆች ናቸው የሚጎዷቸው በማለት ይገልጻል ፡፡

በሀገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተፈጥሮ አደጋው ምክንያት ብቻ ፈጣን እርዳታን ይሻሉ፡፡ የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የሚደርሰውን የዝርፊያ ጥቃት ረጂዎቹ ያገናዘቡ አይመስሉም ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡