የ’አድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ’ በአፍሪካ ህብረት እውቅና አገኘ

በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ – መንበር በአልፋ ኮንዴ እና በህብረት ኮሚሽን ሊቀ – መንበር ሙሳ ፈቂ መህመት በተመራው 29ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዩኒቨርሲቲውን መመስረትና ዓላማውን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለመሪዎቹ ባደረጉት ገለጻ፤ ዩንቨርሲቲው የአፍሪካዊያን መብትና ክብር በሚመለከት የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮች እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሰቲው የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እና አስተሳሰብ የሚሰብኩ ምሁራንን ለማፍራት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

መሪዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተሰጠውን ማብራሪያ ከዳመጡ በኋላ፤ ዩኒቨርስቲው የሚመሰረትበት ዓላማ ህብረቱ ከያዘው እቅድ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑን በመግለጽ ለመመስረቱ እውቅና ሰጥተዋል። 

የፓን አፍሪካን ዩንቨርሲቲ የአድዋ 121ኛ የድል በዓል በተከበረ ማግስት ሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቪኒ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪና የታሪክ ምሁራን፣ አርበኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።

በወቅቱም ዩኒቨርስቲው “የኢትዮጵያን ገድል ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካን የቀኝ ግዛት ታሪክ የማስተማርና የምርምር ስራ የሚዳስስ" እንደሚሆን መገለጹ ተዘግቧል።

ዩኒቨርስቲው የሚያርፈው 100 ሺ ሄክታር ላይ ሲሆን፤ ግንባታው የኢትዮጵያ መንግስትና ለጥቁሮች መብት ተሟጋቾች በሚያወጡት ገንዘብ እንደሚካሄድ ተመልክቷል።

የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩንቨርሲቲ ግንባታ አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ የዩንቨርሲቲው የህንጻ ዲዛይን ሥራና የግንባታ ጨረታ ሂደት እስከ መስከረም 2010 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በጥቅምት 2010 ዓ.ም እስከ አንድ ሺ የሚሆኑ ከአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ከመላው ዓለም የተውጣጡ የጥቁር ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ስለ ዩኒቨርሲቲው ቀጣይ አቅጣጫ የሚመክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ።

የዩኒቨርሲቲው ግንባታ በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ በ2012 ዓ.ም የትምህርት መስጠት መርሃ ግብሩን እንዲጀምር እቅድ ተይዟል-(ኢዜአ)።