የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ፍሬያማ ውይይት ተካሂዶበታል- ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ

ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ፍሬያማ ውይይት የተደረገበት መሆኑን የጊኒ ፕሬዝደንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር አልፋ ኮንዴ ገለጹ።

አልፋ ኮንዴ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው እንገለጹት፤ ውይይቱ አፍሪካዊያን ለጋራ ችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በአንድ ድምጽ እንዲናገሩ ያስቻለ ነበር።

የወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በአጉሪቷ ሰላም ማስፈንና ሕብረቱ በፋይናንስ እንዴት ይጠናከር የሚሉ ሃሳቦች የጉባኤው ዋነኛ የመወያያ  አጀዳዎች ነበሩ።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት አጀንዳዎች የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች ለዓላማው መሳካት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

ህብረቱን በፋይናንስ ለማጠናከር በተረቀቀውና ሁሉም አባል አገራት ከዓመታዊ ገቢያቸው 0 ነጥብ 2 በመቶ እንዲያዋጡ በሚጠይቀው ሃሳብ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ጉዳዩ ላይ ትኩረቱን አድሮጎ የሚሰራ 10 ሚኒስትሮችን ያካተተ ኮሚቴ መዋቀሩንም ገልፀዋል ሊቀመንበሩ።

የላይቤሪያዋ ፕሬዚዳንት ኤለን ስርሊፍ ጆንሰን በበኩላቸው ጉባኤው የተሳካና ከመቼውም ጊዜ በላይ የአፍሪካዊያንን አንድነት ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ጉባኤው በሠላም እንዲጠናቀቅ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

"ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ጀምሮ ለአፍረካዊያን አንድነትና ስኬት ሳትታክት እየሰራች ያለች አገር!" በማለት ኢትዮጵያን አሞካሽተዋታል።

አፍሪካዊያን በአንድ ድምጽ እንደ አንደ አገር መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ያወሱት ሰርሊፍ ጆንሰን፤ ይህም በ2063 የበለጸገች አፍሪካን ለመንገንባት የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያሳልጠው ጠቁመዋል።

አዲስ የተሾሙት የህብረቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ቪክተር ሃሪሰን እና የሰው ሃብት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነር ሳራህ አያንግ አግቦር ቃለ መሃላም የጉባኤው የመዝጊያ ስነ-ስርዓት አካል ነበር (ኢዜአ) ።