በትግራይ ከ7ሺህ በላይ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የማስጠንቀቂያና ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ

እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ በሆኑ ከ7 ሺህ 700 በላይ የመንግስት አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ የመስጠንቀቂያና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ አስታወቁ ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የ2009 ዓ.ም የስራ አፈጻፀም ሪፖርትን ትናንት በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ባቀረቡበት ወቅት፤ የተወሰደው እርምጃ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ በህግ እስከ መጠየቅ የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለጉባኤው የቀረበው የክልሉ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በዚህ ዓመት ባለፉት 15 ዓመታት የተከናወኑ ስራዎችን መሰረት ባደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲፈተሹ ተደርጓል ፡፡

በዚሁም መሰረት ለ6 ሺህ 467 ማስጠንቀቂያ 1 ሺህ 185 የስራ ሽግሽግ፣ 108 ህጋዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ስድስት ያህል ደግሞ ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉን ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም አብራርተዋል፡፡

ግምገማውን ቀጣይ በማድረግ የአመራሩ እና የሰራተኛውን የህዝብ ወገንተኝነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

በዚህ ዓመት በክልሉ ከሚገኙ 367 ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች ውስጥ 173 ሺህ ያህሉን ወይም ከ47 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ለስራ አጥ ወጣቶች ለሚሰጠው ብድር ከሚከፈለው ወለድ 7 በመቶውን መንግስት በመሸፈን 8 በመቶ ወለድ ብቻ እንዲከፍሉ በመወሰንም 901 ሚሊየን ብር ብድር ለ43 ሺህ ወጣቶች መሰጠቱ ገልጸዋል፡፡

ብድር የወሰዱትን ወጣቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ በማስገባት ሂደት የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በቀጣይ ድጋፍ እና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል ፡፡

በገጠር የግብርና ልማት ሰራዊትን በማጠናከር ሙሉ የግብርና ፓኬጅን ተጠቅሞ በክላስተር የሚያለማ አርሶ አደር ለመፍጠር በተደረገው ጥረት የአነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታማነት የ15 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስረድተዋል ፡፡

ይህን በማጠናከር በ2009/2010 የምርት ዘመን ከ28 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም በጉባኤው ቀርቧል፡፡

በክልሉ 39 ሺህ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች መቋቋማቸውን ተመልክቷል ፡፡

ለማምረቻው ዘርፍ በተደረገው የገበያ ትስስር ወደ ውጪ ከተላኩ እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ከሚተኩ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የተገኘው ገቢ ወደ 13 ቢሊየን ብር ማደጉም በጉባኤው ተገልጿል፡፡

በከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ከ14 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩበት 677 ሄክታር መሬት መሰጠቱን ነው የተመለከተው ፡፡

በሪፖርቱ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በግብርና ግብዓቶች፣ በብድር አመላለስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ላቀረቡት ጥያቄ ዛሬ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ የጀመረውን የክልሉን ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በመጪው አርብ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል -(ኤፍ ቢ ሲ) ፡፡