የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በሱዳን ካርቱም ከዛሬ ጀምሮ የሦስት ቀናት ኦፊሴላዊ ጉብኝት እንደሚያደርግ የሱዳን ፕሬዚደንት የፕሬስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።
ጽህፈት ቤቱ ከትናንት በስተያ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በአካባቢያዊ ፣ ዓለም አቀፍና በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም በሱዳን ጉብኝታቸው ከሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑት ባካሪ ሃሰን ሳሊህ ጋር እንደሚወያዩም ተገልጿል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በሱዳን ቆይታቻው ካርቱም በሚገኘው የፍሬንድሺፕ አዳራሽ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉብኝታቸው በሱዳን የባህል ትርኢት ላይ በተጋባዥነት የሚገኙ ሲሆን በሱዳን የኢንዱስትሪ ማዕከላትንም እንዲጎበኙ በወጣው መርሃ ግብር ተመልክቷል ።
በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም በተመራው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የባለሥልጣናት የልዑካን ቡድንም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ፣ የውሃ ፣ የመስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር አቶ ስለሺ በቀለ ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ ብርሃነ ክርስቶስ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚንስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አብረው ተጉዘዋል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት በፖለቲካው ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በወታደራዊ ዘርፎች ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል ።
ሁለቱ አገራት በተለይ በድንበር አካባቢ የተቀናጁ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በማድረግ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፈው ሚያዚያ ሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ግንኙነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሁለቱ መንግሥታት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎችን ግንኙነታቸው እንዲዳብር የሚያስችል ስምምነትም ባለፈው የካቲት ወር ላይ መደረሱ ይታወቃል ።
የሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያ ለምትገነባውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፉን መግለጹ ይታወሳል ።
እኤአ በጥቅምት 2016 ሁለቱ አገራት በፀጥታንና ወታደራዊ መስኩ ትብብራቸውን ለማጠናከርና ሽብርተኛነትን በጋራ ለመዋጋት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል ።( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን )