የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስተኛ ምርጫ 3ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነገ እንደሚጀመር አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ጁል ኛንጋል ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባኤው ከጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።
በሁለት ቀናት ቆይታውም በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የልማትና መልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከእዚህ በተጨማሪ የሁለተኛው ግማሽ ዓመት የክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ላይ ተወያይቶ አቅጠጫ ማስቀመጥና ሰባት የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ጁል አስረድተዋል።
በጉባኤው የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች ተወካዮችን ጨምሮ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። (ኢዜአ)