ወጣቱ የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይኖርበታል- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም

ወጣቱ ትውልድ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት ላይ የነቃ ተሳትፎና ትግል በማድረግ የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይኖርበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ በንግግር  ሲከፍቱ ነው፡፡ ለሁለት ቀን በሚካሄደው ሰብሰባ ላይ ከፍተኛ የሀገሪቱ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በፈጣን እድገት ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የህብረተሰብ ፍላጎት መጨመር የታየበት መሆኑን የገለጹት  ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል አቅም ለመፍጠር ትግል የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን” ብለዋል።

የጨመረውን ፍላጎት ያህል ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ ማርካት አለመቻልን እንደ ችግር ጠቅሰዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በጀማሪ ካፒታሊዝም የእድገት ደረጃ የሚያጋጥም እንደሆነም አስረድተዋል።

ወጣቱ ትውልድም በዚህ መድረክ ላይ የነቃ ተሳትፎና ትግል በማድረግ የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይኖርበታል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ሃለማሪያም

የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ጥበቡ በቀለ በበኩሉ ሊጉ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት የደረስንበት ሁለንተናዊ የመዋቅር ጥንካሬ ይበልጡን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግሯል።

የአዲስ አበባ ወጣት ዛሬ ላይ ያሳየውን ተሳታፊነትና የባለቤትነት መንፈስ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም ሊጉ እንደሚሰራ ገልጿል።