ባለፈው ሰኞ የተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያገኘችበት እንደነበር የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ 30ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ ዘርፎች ተጠቃሚ እንድትሆን ከማስቻሉም በላይ በገጽታ ግንባታ ረገድ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል ።
30ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአጠቃላይ 10 ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት እንዲሁም ተቋማት ልዑካን ቡድን አባላት የተገኙበት በመሆኑ ከፍተኛ ተሳታፊዎችን በማስተናገድ ረገድ ቀዳሚው የመሪዎች ጉባኤ ሆኖ ተመዝግቧል ።
በጉባኤው 678 የሚሆኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ተገኝተው መዘገባቸውን የጠቆሙት አቶ መለስ ከኒዎርክ በመቀጠል ከፍተኛ የአገራት የጎንለጎን ውይይቶች የተካሄደበት ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ እንደ ሦስት አገር ሳይሆን እንደ አንድ አገር በመሆን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በመሪዎች ደረጃ ውይይት እንዲያደርጉም ጉባኤው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አቶ መለስ አለም አያይዘው ገልጸዋል ።
ጉባኤው በተካሄደባቸው ቀናት የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ላሳየው ጨዋነት የተሞላበት አቀባበልና መስተንግዶ እንዲሁም ትብብር በአፍሪካ መሪዎች ጭምር የተደነቀ መሆኑ ያወሱት አቶ መለስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለጉባኤው ስኬታማነት ላደረገው አስተዋጽኦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስጋና ማቅረቡን ተናግረዋል ።
30ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአጠቃላይ ከ55 የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ውስጥ 49 የሚደርሱ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት መሪዎች መሳተፋቸውን ዋልታ ሚዲያናኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል ።