በሀላባ ልዩ ወረዳ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለመደገፍ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

በሀላባ ልዩ ወረዳ በቁሊቶ ከተማ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ለመደገፍ እና ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና ለማቅረብ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡   

ባለፉት ሶስት አመታት የልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ኑር ሰልሃ  በሃላባ  ልዩ ወረዳ ላከናወኑት የልማት ተግባራትን ለማድነቅና ምስጋና ለማቅረብ  የድጋፍ  ሰልፉ የተዘጋጀበት ሁለተኛ ዓላማ  መሆኑ በሰልፉ ላይ ተገልጿል ።  

 የልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኑር ሰልሃ ባደርጉት ንግግር በሀገሪቱ እየመጡ ላሉ የአንድነት፣ የፍቅርና የልማት ስራዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ለመሆን የድጋፍ ሰልፉን ላከናወኑት አካላትና በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለተገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል ፡፡

የሀገሪቱ አሳቢና ተቆርቋሪ በመምሰል የተጀመረውን ልማትና መነቃቃት ለማስቆም እንዲሁም በሀገሪቱ ግጭቶች በዝተው ሠላምና ልማት በማጣት ሀገሪቱ ልትበታተን ጫፍ ደርሳ እንደነበረ ያስታውሱት አስተዳደሪው መሪ ድርጅት ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን አመራሩን ከማጥራት ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰድ የሄደበት ርቀት ፍሬ ማፍራቱን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ህብረተሰቡ ለምስጋና ለመውጣት መጀመሩ እንደማሳያ መወሰዱንና ይህንንም ለማስቀጠል የሀላባ ልዩ ወረዳና የቁሊቶ ከተማ ነዋሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉ  አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በሰልፉ ላይ የተሳተፉት የሀላባ ልዩ ወረዳና የቁሊቶ ከተማ ህብረተሰብ ክፍሎች ዶክተር አብይ እያመጧቸው ባሉ ለውጦች ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው መደመርን ከቃላት ባለፈ በተግባር  ልናውለው ይገባናል ብለዋል፡፡

ይህንንም ልዩ ወረዳው ተግባራዊ እያደረገ ነው ሲሉ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ለልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው  እያገለገሉ ላሉት  አቶ መሐመድ ኑር ሰልሃ በወረዳዋ  የልማት ለውጦች እንዲመዘገቡ  ላደረጉት  አስተዋጽኦ ከህብረተሰቡ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡