በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ግጭት መከሰቱ ተገለጸ

በኢትዮጵያናሱዳን  ድንበር አካባቢ ግጭት መከሰቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም እንደተናገሩት በአካባቢው ግጭት የተከሰተው የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበትን የእርሻ መሬት እንዳያርሱ በመከልከላቸው ነው ።

እንደ አቶ ዘላለም ገለጻ በድንበሩ አካባቢ ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያ አርሶአደሮች እያረሱበት የሚገኝ መሬት  በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች መካከል የግጭት  መንስኤ የሆነው ።

በአሁኑ ወቅት የሱዳን አመራሮች “ የእርሻ መሬቱን መጠቀም ያለብን እኛ ነን ” የሚል  ሃሳብ እያቀረቡ  ነው ያሉት አቶ ዘላለም ሃሳቡ ተገቢነት የሌለው መሆኑን  ለአካባቢው የሱዳን አመራሮች አስረድተናል ብለዋል ።

የሱዳን አመራሮች ጉዳዩን በተመለከተ ያቀረብነውን ሓሳብ ባለመቀበላቸው መግባባት  እንዳልተቻለም አቶ ዘላለም አያይዘው ገልጸዋል ።   

የግጭት ምክንያት የሆነው  ቦታ በኢትዮ-ሱዳን በመተማ ወረዳ ደለሎ ቁጥር 4 የእርሻ እና የኢንቨስትመንት ቦታ እና በሱዳን ባሶንዳ ዞን መካከል በሚገኝ  መሆኑ  ተጠቅሷል፡፡

በግጭቱ ምክንያትም በሁለቱም ወገን የሰው ህይወት መጥፋቱንና የቆሰሉም መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ግጭቱ እንዳይባባስና በአካባቢው መረጋጋት ለመፍጠር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት በሥፍራው እንዲሠማሩ መደረጉን አስተዳዳሪው ተናግረዋል ።

በጉዳዩ ላይ  እስካሁን ምንም ዝርዝር መረጃ አለመኖሩንም  ጭምር  የአማራ  መገናኛ ብዙሃን  ድርጅት ዘግቧል።