ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያወውያንን ሊያወያዩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የሁለት ቀን ውይይት ሊያደርጉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር አስታወቀ።

መድረኩ ሐምሌ 21 እና 22 ቀን 2010ዓ.ም በዋሽንግተንና በሎሳንጀለስ ከተሞች በቅደም ተከተል የሚካሄድ ሲሆን “ግንቡን እናፈርሳለን ድልድዩን እንገነባለን” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ይሆናል።

በውይይቱ ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዘር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከት ሳይወስነው መሳተፍ እንደሚችልና የሚተላለፈው መልዕክትም በማንኛውም አገራት የሚኖሩ ሁሉም ዲያስፖራዎች የሚወከሉበት ነው ሲሉ የመድረኩ ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ ገልፀዋል።

መድረኩን የሚያስተባብር ኮሚቴ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ተቋቁሞ በቂ ዝግጅት መደረጉንና ውይይቱ በዲያስፖራው ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው በአገራቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም በኢትዮጵያ የኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዋናው ውይይት በተጨማሪ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶችና ተወካዮች ጋር ሌላ የጎንዮሽ ውይይት እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራዎች ያሏት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት በሰሜን አሜሪካ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። (ኢዜአ)